የአገው ፈረሰኞች በዓል ገበያውንም አነቃቅቷል።

31

ባሕር ዳር: ጥር 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 85ኛውን የአገው ፈረሰኞች በዓል በደጋማዋ የእንጅባራ ከተማ በድምቀት ለማክበር ሁሉም አይነት ዝግጅቶች ተደርገዋል።

ፈረሰኞች ፈረሶቻቸውን በሚገባ ሸልመው ለመውጣት ቸኩለዋል፤ እናቶች ባሕላዊ ምግቦችን በማዘጋጀት ተጠምደዋል፣ ወጣቶች የከተማቸውን የመንገድ ዳርቻዎች ለማስዋብ ወዲያ ወዲህ እያሉ ነው።

ከዚህ ሁሉ ዝግጅቶች ውስጥ አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ የበዓሉ ድምቀት የኾነውን የባሕላዊ አልባሳት ዝግጅት በከተማው ተዘዋውሮ ተመልክቷል። ሁሉም የባሕል አልባሳት ባለሙያዎች በትዕዛዝ የተሰጧቸውን ልብሶች ለማዘጋጀት እየተጣደፉ ነው።

አቶ መንግሥቱ ምትኩ ለበርካታ ዓመታት በዚሁ የባሕል አልባሳት ሥራ ላይ ተሠማርተው እየሠሩ ይገኛል።

በተለይም ዓመት ጠብቆ የሚከበረው የአገው ፈረሰኞች በዓል በመጣ ቁጥር ከፍተኛ ገቢ እንደሚያገኙበት ገልጸዋል። አቶ መንግሥቱ እንደሚሉት “ሥራዬ ሁለት ነገር ያስገኝልኛል፤ አንድም ኢኮኖሚ ሁለትም ባሕልን ለማሳደግ ይጠቅመኛል”

በዓሉን በባሕላዊ አልባሳት ለማድመቅ ጠንክረው እንደሚሠራም ገልጸዋል። በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሥራ ተቀዛቅዞ እንደነበር የገለጹት አቶ መንግሥቱ የአገው ፈረሰኞች በዓል ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሮልናል ነው ያሉት።

ሌላው የባሕላዊ አልባሳት ባለሙያ ወጣት ወንደሰን አይኔ በተለይም “ጃኖ” የተባለውን ባሕላዊ ልብስ በስፋት ያዘጋጃል። ጃኖን በተለያየ ዲዛይን ለወጣቶች በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ኾኗል።

ወጣት ወንድወሰን ከሰዎች ልብስ ስፌት ቤት ተቀጥሮ ይሠራ ነበር። በ83ኛው አገው ፈረሰኞች በዓል ላይ የተለየ የጃኖ ዲዛይን አዘጋጅቶ ከጓደኞቹ ጋር ለብሶ በመውጣት ማሳየቱን ያስታውሳል።

ልብሱ በዚሁ በዓል ላይ ታይቶ ተወደደለት። ከዚያ በኋላም “ለኔም ሥራልኝ” የሚሉ ወጣቶች በዙ ይላል ወጣቱ።

ይህንን ተከትሎም የራሱን ልብስ ስፌት ቤት ከፍቶ መሥራት ጀመረ። አሁን ላይ ለ3 ወጣት ባለሙያዎች ጭምር የሥራ እድል በመፍጠር በርካታ የባሕል አልባሳትን በማዘጋጀት ላይ ይገኛል። የወጣት ወንድወሰንን ኢኮኖሚ የአገው ፈረሰኞች በዓል የወለደው ነው ማለት ይቻላል።

አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ያነጋገራቸው ባሕል አልባሳት ሸማቾችም በዓሉን በድምቀት ለማክበር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኮምቦልቻ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል።
Next articleየጸጥታ ተቋማት የውይይት መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ እየተካሄደ ነው።