የኮምቦልቻ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል።

26

ደሴ: ጥር 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ ከ515 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት እየተገነባ ነው። የፌደራል እና የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በቦታው ተገኝተው የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

በጉብኝቱ የተገኙት የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር) እንደተናገሩት ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። ግንባታው በመልካም የአፈጻጸም ደረጃ ላይ ይገኛል ያሉት ሚኒስትሩ ሥራው በዚህ ዓመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለከተማው ሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ይኾናል ሲሉም አረጋግጠዋል።

ቢሮው የከተሞችን የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሳደግ በትጋት እየሠራ ነው፤ የኮምቦልቻ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም አንዱ ማሳያ ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) ናቸው።

ፕሮጀክቱ የነዋሪዎቹን የንጹህ መጠጥ ውኃ እጥረት ሙሉ ለሙሉ ይቀርፋልም ብለዋል። ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ማኅበረሰቡ ዘላቂ እና አስተማማኝ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽ እንደሚኾንም አረጋግጠዋል።

የውኃ ልማት ሥራ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ተልዕኮ ሳይሆን በማኅበረሰቡ እና ባለድርሻ አካላት ተዋናይነት የሚሳካ ተግባር ነው ብለዋል ቢሮ ኀላፊው።

በተለይም ኅብረተሰቡ ከግንባታ ጀምሮ እስከ ማሥተዳደር እና የተቋማትን ዘላቂነት እስከማረጋገጥ ድረስ ሚናው የጎላ ነውም ብለዋል። በዚህ ፕሮጀክት የማጠናቀቂያ የሥራ ሂደትም የመላው ተጠቃሚ የላቀ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሰይድ ሁሴን በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በ2014 ዓ.ም የተጀመረ ቢኾንም የሰሜኑ ጦርነት እና ሌሎች ሳንካዎች ፈተና ኾነውብን ነበር ብለዋል።

ይሁን እንጂ ከጥር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ግንባታው በከፍተኛ ግለት ተከናውኖ ለዚህ የማጠናቀቂያ ሰዓት ደርሰናል፤ በያዝነው የበጀት ዓመትም ቀሪ ተግባራት ተጠናቀው ፕሮጀክቱ ለአገልግሎት ክፍት ይኾናል ሲሉ አብራርተዋል።

250 ሺህ ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርገው ፕሮጀክቱ በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ውኃ ልማት ፈንድ የረጅም ጊዜ ብድር እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

ግንባታው ሲጠናቀቅ የከተማውን የውኃ ሽፋን ከነበረበት 61 በመቶ ወደ 100 ከፍ ያደርገዋል ነው ያሉት።

700 ሜትር ኩብ ውኃ የመያዝ አቅም ያለው የማጠራቀሚያ ጋን እና 5 ሺህ ሜትር ኩብ የመግፋት አቅም ያለው ግፊት ጣቢያም ተሠርቶለታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበእስቴ ወረዳ ሕዝባዊ የሰላም ውይይት ተካሄደ።
Next articleየአገው ፈረሰኞች በዓል ገበያውንም አነቃቅቷል።