ለኢትዮጵያ መጻኢ ዕድል የፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት እና የሕግ መንግሥት አንቀጾች ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ፡፡

172

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 25/2012 ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ሊካሄድ ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የሕዝብን ጤንነት ለማስጠበቅ በተላለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረትም ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንደማይካሄድ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን ሐሳብ የተወካዮች ምክክር ቤት በአብላጫ ድምጽ አጽድቆ፣ ለሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

ሀገር አቀፍ ምርጫ መካሄድ ባለመቻሉ ወረርሽኙን መቋቋም እስከሚቻልና ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ሀገሪቱን ለማስተዳደርም አራት የቢሆን አማራጮችን ከሰሞኑ ቀርበዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ ሕገ መንግሥት ማሻሻል እና ሕገ መንግሥትን መተርጎም የሚሉ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦች ናቸው በጥናት ተደግፈው የቀረቡት፡፡ በዚህ ጉዳይ አብመድ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎችን አናግሯል፡፡

የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኑር ወለላ ‘‘በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የምርጫው መራዘም ሕዝብን ለማዳን ትክክለኛ አማራጭ ነው’’ ብለዋል፡፡ ፓርቲያቸው ከተመላከቱት ቢሆኖች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅና ምክር ቤቱን መበተን የሚሉት አማራጭ ሐሳቦች የየራሳቸው ውስንነቶች ያሉባቸው በመሆናቸው ‘‘ለችግሩ ሁነኛ መውጫ መንገድ አይሆኑም’’ ብሎ እንደሚያምን ተናግረዋል፡፡

ምንም ዓይነት የሐሳብ መቀራረብ የማይታይባቸውና በራሳቸው ጫፎች ላይ የቆሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ሳይኖራቸው የሽግግር መንግሥት መሥርተው ካለው ወረርሽኝ አንጻር ሀገር ለመምራት በእጅጉ ከባድ እንደሚሆንም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከችግሩ ለመውጣት የሚቻለው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58 (3) ላይ የቀረበውን ድንጋጌ በማሻሻል እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀ መንበርና የመድረክ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት በየነ ጲጥሮስ (ፕሮፌሰር) የምርጫው መራዘም በሀገር ጥቅምና በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲሠራ የግድ እንደሚል ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ካቀረባቸው አራት ሐሳቦች አንፃር በሕገ መንግሥቱ የሚሻሻሉ አንቀፆች በሰላማዊ አግባብ እስኪፈቱ ባለው ማዕቀፍ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ሁነቱ የምርጫ እንቅስቃሴን የሚገድብ በመሆኑ በመንግሥት የቀረቡ አራቱ አማራጮች የየራሳቸው ጠንካራ እና ደካማ ጎን እንዳላቸውም ፓርቲያቸው እንደሚያምንም ተናግረዋል፡፡
ሀገሪቷን እንደሀገር ለማስቀጠል የፖለቲካ ፓርቲዎች በሐሳብ ስለተቃረኑ የሚያሰጋ ሊሆን አይገባም፤ የፖለቲካ ሥራ ላይ አስተዳደራዊ ጫና ቢኖርም ሀገር በሕዝቦች ስምምነት የቆመች መሆኗን መረዳት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የቀረቡት አማራጮች የሀገር ውስጥ ማሻሻያዎች ለማድረግ አለማስቻልና ከሀገር ውጭ ከሚኖር ግንኙነት እና ተፅዕኖ አንጻር ለመቋቋም የሚያስችሉ አለመሆናቸው ነጻ የፓርቲዎች እንቅስቃሴን በመፍቀድ በፖለቲካዊ ስምምነት መፍታት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡
ፕሮፌሰር በየነ የሕገ መንግሥት ትርጓሜን ከዚህ በፊት ከተቀመጡ አንቀፆች ውጭ ለሕዝብ ጥቅም እና ለሀገር ሉዓላዊነት ሲባል ሰፋ አድርጎ መተርጎም በዓለም ላይ የሚሠራ ልምድ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ ‘‘ስልጣን ላይ ያለ አካል በዚህ ሂዱ ብሎ መወሰን ይችላል’’ ብለዋል፡፡ መንግሥት ይህን በመረዳት ለሀገር እና ለሕዝብ የሚበጅ ጥሩ አማራጭ እንደሚያመጣ ተስፋ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ ሆኖ የምርጫው መራዘም ፓርቲዎች ጥምረት እንዲፈጥሩ፣ እንዲዋሐዱ እና ለሕዝብ የሚበጅ አጀንዳቸውንም እንዲያጠናክሩት እና እንዲከልሱት ዕድል ሊፈጥር እንደሚችልም አንስተዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጣሂር ሙሐመድ ደግሞ ፓርቲው ምርጫው ከመራዘሙ በፊትም እንደሀገር መሠራት ያለባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ያምን እንደነበር አንስተዋል፡፡

አብን የአማራ ሕዝብን ችግር ለመፍታት ከምርጫ በፊት ከክልሉ ውጭ ያሉ ተወላጆች የፖለቲካ ውክልና እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚያስፈልግና የሕዝብ ቁጥርን ማወቅ እና ሀገራዊ ስምምነት መፍጠር ያስፈልግ እንደነበር እንደሚያምንም አቶ ጣሂር ተናግረዋል፡፡

‘‘አሁን ባለው የሕግ ማዕቀፍ ምርጫ አራዝሞና ሕጋዊ መንግሥት ሆኖ መቆየት አይቻልም፡፡ ሁለት ምርጫ አለ፤ ‘በፖለቲካ ድርድር አማካኝነት በባላአደራ የሽግግር መንግሥት ወይስ ፓርላማው ተበትኖ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የኃይል ገደብ መቀጠል አለበት?’ የሚል ስምምነት ያስፈልጋል’’ ነው ያሉት፡፡

ከቀረቡ አራት አማራጮች ውስጥ ፓርቲያቸው የመጨረሻ ውሳኔ በቅርቡ እንደሚያሳልፍ የገለጹት አቶ ጣሂር ‘‘ከቀረቡት አማራጮች ግን በሕገ መንግሥቱ የሚሻሻሉ አንቀፆች ላይ መግባባት ቀዳሚው ነው’’ ብለዋል፡፡ ማሻሻያዎችን ለሕዝቡ ይፋ ማድረጋቸውንም ነው የገለጹት፡፡
እንደ አቶ ጣሂር ገለጻ አብን ሀገሪቱ በውጭ ኃይልና በኢኮኖሚ ድቀት ተፅዕኖ ውስጥ እንዳትገባ ማዕከላዊ መንግሥቱ እንዲጠነክር ፍላጎት አለው፤ ነገር ግን መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጠቀም ጫና እንዳይፈጥር የፓርቲዎችን ስምምነት መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ አስካሁን ባለው ማዕቀፍ በፖለቲካዊ ውይይትና በአማራጭ በፖለቲካ ድርድር ካልሆነ በሕገ መንግሥቱ አግባብ ቀጣዩን ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻልም አስታውቀዋል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚወሰዱ ርምጃዎችና የሚጣሉ ገደቦች (ቤት መቀመጥ፤ አለመሰብሰብ፤ አለመንቀሳቀስ፤ አካላዊ ፈቀቅታ…) ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ የማድረግ አቅምን ስለሚፈታተኑ ውሳኔውን ለማስተግበር ሁሉም ፓርቲዎች እንደሚሠሩም ተናግረዋል::

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የዜጎች ነጻነትና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ የሚገደብ በመሆኑ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ስለማይፈጥር የፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት ከአዋጁ ማግስት ሊካሄድ ከታሰበው የምርጫ ውጤታማነት አንጻር ከፍተኛ እገዛ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ እስከ ዛሬ ድረስ የ51 ሀገራትና የክልሎች ምርጫ መራዘሙን ታውቋል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

Previous articleበቫይረሱ የተያዙም ሆነ ምልክቶች የታዩባቸው ሰዎች የሚመዘገቡበት ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ተሠራ።
Next articleስድስት ሰዎች ሲያገግሙ ሁለት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ።