
ባሕር ዳር: ጥር 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጥር ወር ከሚከበሩ በዓላት መካከል ፈረሰኞች የሚታደሙባቸው ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት ይጠቀሳሉ። ምንም እንኳ በርካታ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት በፈረስ እና ስፖርቱ የሚታጀቡ ቢኾንም የጥር 23ቱ የአገው ፈረሰኞች ማኅበር፣ የጥር 25ቱ የደብረታቦር እና የእስቴ-መካነኢየሱስ ፈረሰኞች ውድድር እና ትርኢት ደግሞ ጎላ ብለው የሚከወኑ ኹነቶች ናቸው፡፡
የእስቴ መካነኢየሱስ ፈረሰኞች እና ኅብረተሰቡ ዘንድሮም የጥር 25/2017 ዓ.ም የመርቆሪዎስ በዓልን በድምቀት ለማክበር ተዘጋጅተዋል፡፡ አቶ ተስፋ አያሌው የመካነኢየሱስ ፈረሰኞች ማኅበር አባል ናቸው፡፡ ዘንድሮ የመርቆሪዎስ በዓልን በድምቀት ለማክበር እየተዘጋጁ መኾኑን አንስተዋል።
ማኅበራቸው 35 አባሎች ያሉት ሲኾን በሕግ እና ደንብ ይመራል፡፡ ለበዓሉም መለያ ልብሳቸውን በማሰፋት፣ የጋራ ወጭያቸውን የሚሸፍኑበት አማራጭ በማፈላለግ እና የፈረስ ግልቢያ ልምምድ በማድረግ እየተዘጋጁም ነው፡፡ በ1992 ዓ.ም የተቋቋመው ማኅበራቸው የመርቆሪዎስ በዓልን ከማክበር በተጓዳኝ በወረዳቸው እና በክልሉ በሚደረጉ ስፖርታዊ ውድድሮችም ይሳተፋል፡፡
አቶ ተስፋ በፈረስ ሽርጥ እና ጉግስ ለመወዳደር እንዲኹም ታቦቱን ለማጀብ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በዓሉ ሲጠናቀቅም እንግዶችን ለማስተናገድ እና ተመራርቀው ለመለያየት ዝግጅት እየተደረገ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡ በፈረስ ትርዒቱ እና ውድድሩ ግጭት እና ጉዳት እንዳይኖር አስቀድሞ ምክክር እንደሚደረግ ነው አቶ ተስፋ የተናገሩት፡፡
በጦር ውርወራ እና በመሳሰሉት ውድድሮች እና ትርዒቶች አስፈላጊው ጥንቃቄ እና ስልትን መጠቀምም የተለመደ ነው፡፡ ዘንድሮም ሰላማዊ እና ጉዳት አልባ ትርዒት እና በዓልን ማክበር እንዳሰቡም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የጸጥታ ኀይሉም ለበዓሉ ሰላማዊነት እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ሌላኛው የእስቴ ፈረሰኛ አቶ ጌትነት በላይ የስምንቱ ፈረሰኞች ማኅበር ሠብሣቢ ናቸው፡፡ በዓሉን በመልካም ኹኔታ ለማክበር ስምንቱ ማኅበራት በሙሉ ልብስ እና ከብቶቻቸውን አሳምረው እንዲመጡ እየተነጋገርን ነው ብለዋል፡፡
ከባሕል እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ጋርም የመተባበር ጅምር መኖሩን ገልጸዋል፡፡ አቶ ጌትነት በበዓሉ በሚደረግ የፈረስ ውድድር እና ትርዒት ግጭት እንዳይኖር ኅብረተሰቡ በኀላፊነት ኹነቶችን እንደሚቆጣጠር ገልጸው በተጨማሪ ግን የጸጥታ ኀይሎች እገዛ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ተናግረዋል፡፡
በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ወንድም ወገኖቻችን በበዓሉ ተገኝተው ቢመለከቱን ደስ ይለናል፡፡ በሌሎች ግንኙነቶቻችንም የበለጠ ጠቀሜታ አለውና መጥታችሁ እዩን ብለዋል አቶ ጌትነት፡፡ የመካነኢየሱስ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች፣ ስፖርት፣ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አዳነ ዓለምነው በከተማቸው ስምንት የፈረሰኞች ማኅበር መኖራቸውን ገልጸው በዓሉን ለማክበር የፈረሰኞች ማኅበርን አወያይተን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
ለፈረሰኞቹም አስፈላጊውን መስተንግዶ እና የመካነኢየሱስ ከተማ እና የእስቴ ወረዳ ነዋሪዎች ለበዓሉ የሥነ ልቦና እና የቁሳቁስ ዝግጅት እንዲያደርጉ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የበዓሉን ማክበሪያ አካባቢዎች እና መንገዶች የመጥረግ እና የማጽዳት ሥራ መሠራቱንም ጠቅሰዋል፡፡ ለበዓሉ የፈረስ ሽርጥ እና የጉግስ ውድድሮች ዋንጫ ተዘጋጅቷል፡፡
የፈረስ ውድድሩ እና ትርዒቱ ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓቱ ጋር ተዋህዶ እና ተናቦ ይፈጸማል፡፡ የየአድባራቱ ካህናት እና አማኝ እንዲገኝ ለሕዝቡም ለሃይማኖት አባቶችም ተነግሮ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል አቶ አዳነ፡፡
በዓሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን ቅድመ ዝግጅት መደረጉን እና ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መኾኑንም ነው አቶ አዳነ የገለጹት፡፡
አቶ አዳነ እስቴ መካነኢየሱስ መርቆሪዎስ በድምቀት እየተከበረ ኅብረተሰቡም ባሕል፣ ታሪክ እና ሃይማኖቱን እንዲያውቅ እና በየዓመቱ እንዲዘክረው የሚደረግበት በዓል በመኾኑ በቅርብም በሩቅም ያሉ ወገኖች በበዓሉ እንዲታደሙ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!