ጥበብ የሚቀዳባት፣ ታሪክ የመላባት- ዋሸራ

117

ባሕርዳር: ጥር 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ውስጥ ወርሐ ጥር የተለያዩ መልኮች አሉት። “ጥር ይደገም” በሚያስብሉ ደማቅ ኹነቶች ታጅቦ ነው የሚያልፈው። ልደትን ዋዜማ አድርጎ፣ ጥምቀትን በያለበት ደምቆ ሀሴትን የሸመተ ያገሬው ሰው እግር ካገጣጠመው ደግሞ ሰባሩ ጊወርጊስን በባሕርዳር የታንኳ ቀዘፋና የጀልባ ትርኢት እየታደመ ከራርሟል።

በጥምቀት ደምቆ ወጥቶ የተቀጣጠረ መገናኛው የአስተርእዮ ማርያም ዕለት ነው። አስተርእዮ ማርያም በደማቅ ኹኔታ ከሚከበርባቸው ታሪካዊ ቦታዎች መካከል ግሸን ደብረ ከርቤ፣ መርጦለ ማርያም፣ ደረስጌ ማርያም እና ደብረ ምዕራፍ ዋሸራ ማርያም ተጠቃሾች ናቸው።

አስተርእዮ ማርያም በደብረ ምዕራፍ ዋሸራ በብዙ መልኩ ይለያል። በርካታ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በደብረ ምዕራፍ ዋሸራ ይከትማሉ። የቅኔ ምንጩ እዚያው ነውና በሊቃውንት ዜማ እና ዝማሜ ታጅቦ የቅኔ ጥበብ እና ምስጢር ይጎርፍበታል።

ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተሠብሥበው ቅኔን ሲያመሰጥሩ የከረሙ የዋሸራ የአብነት ተማሪዎች ከመምህራን እና ሊቃውንት ጎን ቆመው የቀሰሙትን ቅኔ ለታዳሚው ይቀኛሉ። በአስተርእዮ በዓል ዋሸራ የጥር ልዩ ሙሽራ ኾና ትውላለች። ደብረ ምዕራፍ ዋሸራ ማርያም የመጀመሪያው የቅኔ ዩኒቨርሲቲ ባለቤት ናት። መገኛዋም ጎጃም ጎንጅ ቆለላ ወረዳ ውስጥ ነው።

ከአዲስ አበባ በ426 ኪሎ ሜትር ፣ ከባሕርዳር ደግሞ በ82 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ የቅኔ ማሕደር ናት። የጎንጅ ቆለላ ወረዳ ቤተ ክህነት መረጃ እንደሚያመለክተው ዋሸራ ማርያም ገዳም ለመጀመሪያ ጊዜ የተመሠረተችው በ900 ዓ.ም ነው። ገዳሟ የተመሠረተችው አሁን ካለችበት ቦታ በ3 ኪሎ ሜትር ርቀት “ቁራ ገደል” በተባለ ቦታ ላይ እንደነበር ይነገራል። የአሁኗ ደብር ደግሞ አባ ተስፋ ማርያም የሚባሉ አባት ሕንጻ ቤተክርስቲያን አንጸው በ1427 ዓ.ም ነው የመሠረቷት።

“ዋሸራ” የሚለውን ቃል በተለያዩ የሀገራችን የጥበብ ሥራዎች ላይ እናውቀዋለን። ቅኔ ለመጀመሪያ ጊዜ እዝራ ስቱኤል (ድህሪም) በተባሉ ባሕታዊ የተመሠረተው በዋሸራ ነው ይባላል። ከድህሪም ጀምሮ ከ231 በላይ ሊቃውንት ወንበር ተክለው የቅኔን ጥበብ አስተምረዋል። ተተኪ ሊቃውንት ቤተክርስቲያንንም አፍርተውበታል። ከዋሸራ የወጡ የቅኔ ሊቃውንትም ወደ የአካባቢያቸው በመሄድ ቅኔን አስፋፍተዋል።

በዋሸራ አሁንም ቢኾን ከአብነት ተማሪዎች ጎጆ ጥበብ ይቀዳል። በነ ተዋናይ ቅኔ እየተዋዛ እንደ ጅረትም ይፈስሳል። ዋሸራ የሀገር አንጡራ ሀብት የኾነውን ቅኔ ከደሳሳ ጎጆዎች አውጥታ ከፍ ባለ ሰገነት ላይ ለመሾም እየተሠራ ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ 17ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሂዳል።
Next articleአሚኮ ባለው የፕሮግራም አካታችነት እና የዘገባ ጥራት ምክንያት የብዙ ተቋማት አጋር ኾኖ ቆይቷል።