በቫይረሱ የተያዙም ሆነ ምልክቶች የታዩባቸው ሰዎች የሚመዘገቡበት ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ተሠራ።

158

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ታማሚዎችና ምልክቱን የሚታዩባቸው ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው የሚመዘገቡበት የሞባይልና የዌብ ሳይት አፕሊኬሽን ሶፍትዌር መሥራቱን አሳውቋል፡፡

የሞባይል ሶፍትዌር አፕሊኬሽን በሞባይል በቀላሉ ሊጫን የሚችል ነው። ኢንተርኔት ባለበት አከባቢ ሁሉ ይህ አፕሊኬሽን ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ ከተያዙትም ሆነ ምልክቶች ከታዩባቸው መመዝገብ ያስችላቸዋል ብሏል ኢንስቲትዩቱ።

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ማንነትና ያሉበትን ቦታ ለዋና ማዕከሉ ለማሳወቅ ማስቻልም ከጥቅሞቹ መካከል እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡ ቫይረሱ በሚገኝባቸው ጊዜም የተነካኳቸው ሰዎችና የሄዱበትን ቦታ ለመለየት ያስችላል፡፡

ይህም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የነበራችውን ንክኪ እና የቆዩባቸውን ቦታዎች ለማወቅ የሚደረገውን ምርመራ እና የማጣራት ሥራ ቀላል እንደሚያደርገው ታምኖበታል።

ሁለተኛው የዌብሳይት አፕሊኬሽን ሰዎች ምልክቱ ከታየባቸው ጊዜ ጀምሮ በዌብሳይቱ በመግባት የሚመዘገቡበትና በየጊዜው ያሉበትን ደረጃ የሚያሳውቁበት አፕሊኬሽን ነው፡፡

የፈጠራ ሥራው ባለሙያዎች አፕሊኬሽኖችን አገልግሎት ላይ ለመዋል በእያንዳንዱ ዜጋ ሞባይል ላይ መጫን እንዳለባቸው በመግለፅ ለተግባራዊነቱም የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም የፈጠራ ሥራውን ቶሎ ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስፈልገውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ማረጋገጡን ከሚኒስቴሩ ማኅበራዊ የመረጃ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሰሎሞን በላይ( ዶክተር) ከነዚህ ሥራዎች በተጨማሪ በሀገሪቱ ያለውን የአጋዥ መተንፈሻ (ቬንትሌተር) እጥረት ለመቅረፍ በራሳቸው ዲዛይን አንድ ቬንትሌተር፣ ለዩኒቨርሲቲዎች ለማስተማሪያነት የሚያገለግለው 8 ኢንች ቴሌስኮፕ እና 3ዲ ፕሪንተር መስራታቸውንና እነዚህን በብዛት የማምረት ሥራም በቅርብ ጊዜ የሚጀምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ከአየር ንብረት እና መልከአምድር አንፃር ያለው ባህሪይ ምን እንደሚመስል ቡድን በማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ምርምር እየሠራ እንደሆነም ዶክተር ሰሎሞን አስረድተዋል፡፡

Previous articleርእሰ መሥተዳድሩ በሰሜን ሸዋ ዞን የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የመስኖ ልማት እንቅስቃሴን ጎበኙ፡፡
Next articleለኢትዮጵያ መጻኢ ዕድል የፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት እና የሕግ መንግሥት አንቀጾች ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ፡፡