
ሁመራ: ጥር 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትምህርት መምሪያ የ2017 ዓ.ም የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በርካታ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች በኾነ ሁኔታ እያስተማሩ መኾኑን የገለጹት በዞኑ ትምህርት መምሪያ የትምህርት ልማት ስታትስቲክስ ትንተና ዕቅድ ዝግጅት እና ሃብት ማፈላለግ ቡድን መሪ ሙሉብርሃን በላይ ናቸው።
በዳስ ጥላ ሥር የሚማሩ በርካታ ተማሪዎች በዞኑ መኖራቸውንም ቡድን መሪው ጠቅሰዋል። አሁን ያለውን ችግር ለመፍታት የመንግሥት ድጋፍ ብቻ በቂ አይደለም ብለዋል።
የበጀት እጥረት የትምህርት ቁሳቁስ እና በቂ የሰው ኃይል ለማሟላት እንቅፍት እንደኾነባቸው የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ገብረማርያም መንግሥቴ ተናግረዋል። ሁሉንም ወረዳዎችን ተዘዋውሮ ለመደገፍ አስቸጋሪ እንደኾነባቸውም ነው የተናገሩት።
ችግሮቹን እና እጥረቶችን በመቋቋም ሁሉም ወረዳዎች ባላቸው ዓቅም የመማር ማስተማር ሥራውን በተቀናጀ መንገድ እያስሄዱት መኾኑንም አቶ ገብረማርያም ገልጸዋል። የተማረ ትውልድ ለመፍጠር የሚሠራው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በሰሜኑ ጦርነት በርካታ ትምህርት ቤቶች መጎዳታቸውን ያነሱት አቶ ገብረማርያም እነዚህን ትምህርት ቤቶች ለማሻሻል እና ወደ ሙሉ ሥራ ለማሥገባት የሁሉም አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ከዚህ በፊት የዞኑን የመማር ማስተማር ሥራ በማጠናከር እና የተማረ ትውልድ በመገንባት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላት እና ተቋማት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሌሎች ወገኖችም የተማረ ትውልድ የመፍጠር ሂደቱን እንዲደግፉ አቶ ገብረማርያም ጥሪ አቅርበዋል።
የዞኑ ትምህርት ቤቶች መሠረታዊ ግብዓት እና የቁስቁስ ችግር እንዳለባቸው የውይይቱ ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል። አዲሱ የመጽሐፍ ሥርጭት ለሁሉም ተማሪዎች እንዲዳረስ ጥረት መደረግ እንዳለበትም ጠይቀዋል።
በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባር ተኮር የመማር ማስተማር ዕድል እንዲያገኙ ለማስቻል ቤተ ሙከራ አለመኖሩ ችግር እንደኾነባቸውም ተሳታፊዎቹ አንስተዋል። ከሀገር ውጭ እና ከውስጥ ከሚኖሩ ወገኖች በሚገኝ የሃሳብ፣ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ መፍትሄ ለመስጠት አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!