
ደብረብርሃን: ጥር 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና የስድስት ወር ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር መድረክ በደብረብርሃን ከተማ ተካሂዷል። የሰሜን ሸዋ ዞን ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ነፃነት ንጉሴ በዲጅታል ዘርፍ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠናን ወጣቶች በሚጠበቀው ልክ እየወሰዱ አለመኾኑን ተናግረዋል።
የተቆራረጠ የኢንተርኔት አገልግሎት በመኖሩ ምክንያት ሥልጠናውን ለወጣቶች ተደራሽ ለማድረግ የሚሠራውን ሥራ ፈትኖታል ነው ያሉት። በዞኑ በ2017 በጀት ዓመት ከ17 ሺህ በላይ ወጣቶችን ለማሠልጠን ቢታቀድም ሥልጠናውን ወስደው የብቃት ወረቀትን ያገኙት 2ሺህ 152 ወጣቶች ብቻ ናቸው ብለዋል።
የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሙሉነህ ዘበነ በአማራ ክልል በዚህ ዓመት 191 ሺህ ወጣቶችን ለማሠልጠን ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የኢንተርኔት አቅርቦት ባለባቸው አካባቢዎች የድጋፍ እና ክትትል ሥራ በመሥራት ወጣቶች የኢትዮ-ኮደርስ ሥልጠና እንዲወስዱ የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ 5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ አወንታዊ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ለማስቻል እየተሠራ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!