
ባሕር ዳር: ጥር 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ግብርን በወቅቱ እና በጥራት ለመሠብሠብ እንዲቻል ዘመናዊ ቴክኖሎጅዎችን መጠቀም ግድ ይላል፡፡ በተለይም ግብር ከፋዮች ላይ የሚደርሰውን ውጣ ውረድ ለማስቀረት ከዘመኑ ጋር መራመድ እና አሠራሩን ማዘመን አስፈላጊ ነው።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ በዚህ ረገድ ሥራዎችን እየሠራ ነው። አዳዲስ ቴክኖዎሎጅዎችን በመጠቀም የትግበራ ሙከራ ማድረጉንም አስታውቋል፡፡ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የግብር አወሳሰን፣ አሠባሠብ እና ክትትል የሥራ ሂደት ዳይሬክተር አትንኩት በላይ አዳዲስ ቴክኒዎሎጅዎችን ለመጠቀምም የገቢዎች ቢሮ ከባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ ጋር ስምምነት በመፍጠር የኤሌክትሮኒክስ የግብር መክፈያ (ኢታስ) መተግበሪያ በማበልጸግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህ የግብር መክፈያ የትግበራ ሙከራ በባሕር ዳር ከተማ ከ3ሺህ በላይ የሚኾኑ የግብር ከፋዮች መተግበሪያውን ተጠቅመው ተስተናግደዋል ነው ያሉት፡፡ በዚህም ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር እና ታክስ መሠብሠብ እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሮኒክስ ግብር መክፈያ (ኢታስ) ከፋዮቹ ገቢ ተቋሙ ላይ መምጣት ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ኾነው መክፈል የሚችሉበት መተግበሪያ ነው፡፡ መተግበሪያው በኤስ ኤም ኤስ እና በቴክስት ለግብር ከፋዮች የግብር ታክስ መጠኑ ይገለጽላቸዋል ነው የተባለው።
በፌዴራል ደረጃ እንደ ሀገር “ኢታክስ” የሚል የግብር መክፈያ በማበልጸግ በትግበራ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ ይህ መተግበሪያ በአማራ ክልል በባሕር ዳር፣ በጎንደር፣ በደሴ እና በኮምቦልቻ ላይ ወደ ሙከራ ትግበራ ገብቷል ነው ያሉት፡፡
በዚህም 2ሺህ 110 የሚኾኑ ግብር ከፋዮች መተግበሪያውን በመጠቀም ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አድርገዋል፡፡
ይህንን መተግበሪያ በመጠቀም ግብር ከፋዮች ባሉበት ቦታ ኾነው ፋይል ማድረግ፣ ሪፖርት ማድረግ፣ ግብራቸውን መክፈልም ይችላሉ፡፡ ይህም ጊዜያቸውን ይቆጥባል፣ ከብልሹ አሠራር ነጻ ያደርጋል፣ አሠራርን ያቀላጥፋል፣ ወጭን ይቆጥባል፣ የታክስ ገቢውን ከብክነት በጸዳ መልኩ እንዲሠበሠብ ያደርጋል ነው ያሉት።
በተያዘው በጀት ዓመት ከመደበኛ እና ከከተማ አገልግሎት 71 ጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ መታቀዱን የገለጹት ዳይሬክተሩ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 27 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መሠብሠብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተሠበሠበው ጋር ሲነጻጸር 95 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
በቀሪ የግብር አሠባሠብ ሥርዓቱ አዳዲስ ቴክኒዎሎጅዎችን በመጠቀም ከዚህ በፊት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመድፈን የታቀደውን ግብ ለማሳካት ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!