የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነ ነው።

40

ደሴ: ጥር 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የደቡብ ወሎ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከኦስትሪያ ቀይ መስቀል ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በደሴ ዙሪያ እና ተንታ ወረዳዎች ያከናወናቸውን የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች አስመርቋል። ፕሮጀክቱ ከተሰማራባቸው የሥራ ዘርፎች መካከል የንጹህ መጠጥ ውኃ ግንባታ፣ የአምቡላንስ አገልግሎት፣ ሁሉን ዓቀፍ የገንዘብ ድጋፍ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በሁለቱ ወረዳዎች ለ1 ሺህ ሰዎች ለእያንዳንዳቸው 21 ሺህ ብር በጥቅሉ 21 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል። ለ120 ሴቶች በነፍስ ወከፍ 42 ሺህ ብር በጥቅሉ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍም ተደርጓል። በተጨማሪም በእንስሳት እርባታ ተጠቃሚ ለኾኑ 120 ሰዎች ከ2 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ መደረጉም ተገልጿል።

በአጠቃላይ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ገንዘብ ለአንድ ዓመት ያክል ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየው ድርጅቱ በዛሬው ዕለት የተሠሩ ተግባራትን የቀይ መስቀል ማኅበሩ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት የመስክ ምልከታ እና የምረቃ መርሐ ግብር አካሂዷል። ግንባታቸው ከተጠናቀቁ የውኃ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በድርጅቱ የገገንዘብ ድጋፍ በደሴ ዙሪያ እና ተንታ ወረዳዎች በእንስሳት እርባታ የተደራጁ ማኅበራትንም ምልከታ ተደርጓል።

አሚኮ ያነጋገራቸው በእርባታ የተደራጁ ሴቶች እንስሳትን በማድለብ እና የቁጠባ ባሕላቸውን በማሳደግ ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውን ተጠቃሚ እያደረጉ እንደኾነ ገልጸዋል። ከዚህ በፊት በውኃ እጥረት ይቸገሩ የነበሩ አርሶ አደሮችም በአካባቢያቸው በተሠራላቸው የውኃ ፕሮጀክት ተጠቃሚ እንደኾኑ እና ብዙ እንግልት እንደቀነሰላቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የመሰላል ፕሮጀክት አሥተባባሪ ተስፋሁን ዘውዴ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ከመንግሥት መዋቅሮች ጋር በትብብር እየሠሩ እንደኾነ ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ ከፍተኛ የውኃ እጥረት የነበረባቸውን አካባቢች ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አብራርተዋል።

ዘጋቢ:- ደምስ አረጋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች በገቢ ላይ ለውጥ አምጥተዋል።
Next articleዘመናዊ የግብር መሠብሠቢያ ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀመ መኾኑን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገለጸ።