የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች በገቢ ላይ ለውጥ አምጥተዋል።

29

ባሕር ዳር: ጥር 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ወሎ ዞን አርሶ አደሮች ባለፉት ዓመታት ባከናወኗቸው የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች የገቢ ምንጫቸውን በማስፋት በኑሯቸው ለውጥ ማምጣታቸውን ገልጸዋል። በሰሜን ወሎ ዞን የሀብሩ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ አሕመድ ባለፉት ዓመታት በተከናወነ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ መሬቶች እንዲያገግሙ በማድረግ ለእንስሳት መኖ ልማት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።

በተፋሰስ በለማ ተራራማ ስፍራ ላይ ማንጎ ተክል በማልማት በአራት ዓመታት ውስጥ ከምርት ሽያጭ ከሩብ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዳገኙ ገልጸዋል። በመቄት ወረዳ የእማሙዝ ቀበሌ አርሶ አደር አላቸው ንጉሴ በአካባቢያቸው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና ልማት ሥራ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት በርካታ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎችን አከናውነናል ነው ያሉት።

የተፈጥሮ ሀብት በተሠራበት ስፍራ ላይ የፍራፍሬ፣ የማር እና የጌሾ ልማት በማልማት ከምርት ሽያጭ በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከ300 ሺህ ብር በላይ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል። የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ያስገኘውን ጥቅም በመገንዘብ አሁን ላይ ሥራውን እንደ ባሕል በመውሰድ በየዓመቱ እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የሰሜን ወሎ ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ቦጋለ ሰጤ ባለፉት ዓመታት በሕዝባዊ ተሳትፎ ተጎድቶ የነበረ ሰፊ መሬት በአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ መልማቱን ገልጸዋል። አርሶ አደሮች በለሙ ተፋሰሶች ላይ በተለያዩ የግብርና ልማት ሥራዎች ተሰማርተው ኑሯቸውን እየለወጡ ነው ብለዋል። ተራራዎች በደን መሸፈናቸው እና ከሰውም ኾነ ከእንስሳት ንክኪ ነጻ በመኾናቸው ምንጮች ፈልቀዋል። የፈለቁት ምንጪችም አርሶ አደሮች በጓሯቸው አትክልት እና ፍራፍሬ እንዲያለሙ አድርገዋቸዋል ነው ያሉት።

እንስሳትን በማድለብ፣ ንብ በማነብ፣ በፍራፍሬ እና በደን ልማት ላይ በመሰማራት ከተለያዩ ምርት ሽያጮች ከፍተኛ ገቢ በማግኘት ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማሳደጋቸውን ጠቁመዋል። እንደ ኢዜአ ዘገባ በየዓመቱ የተከናወኑ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች የተፈጥሮ ሚዛንን ከመጠበቅ ባሻገር የሰብል ምርታማነትን እያሳደጉ ነው። የዞኑ አርሶ አደሮች በተፋሰስ ልማት ሥራዎች በንቃት እና በስፋት እየተሳተፈ መኾኑንም አንስተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ብልጽግና ፓርቲ እየገነባው ያለው ኅብረ ብሔራዊ፣ የጋራ እና የወል ትርክት ለነገም ስንቅ የሚኾን ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next articleየኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነ ነው።