
ባሕር ዳር: ጥር 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጀግኖች ለጸናች ሀገራቸው ጸንተዋል፡፡ ለተከበረች ሀገራቸው የተከበረች ሕይወታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ተድላ እና ድሎትን ረስተዋል፡፡ የጠላትን ጎራዴ፣ የጠላትን ጦር እና ሰይፍ ንቀዋል፡፡ ለጥንታዊት ሀገራቸው ደማቸውን አፍስሰዋል፡፡ አጥንታቸውን ከስክሰዋል፡፡ ረሃቡ እና ጥሙን ችለዋል፡፡ ስለ ተከበረች ሠንደቃቸው ሲሉ የመከራ ጽዋን ተጎንጭተዋል፡፡ በደስታዋ ተደስተዋል፡፡ በሀዘኗ አዝነዋል፡፡ ከፊት እየቀደሙ ለክብሯ ቆመዋል፡፡
እንኳን ጀግኖች አርበኞች፣ እንኳን ቃል ኪዳን የተቀበሉ ጀግኖች፣ እንኳን የአባት እና የእናት አደራ ያለባቸው ልበ ሙሉዎች፣ ታማኝ ፈረሶችም ለምለም ሳር ግጠው ላደጉባት፣ በሜዳዋ ለቦረቁባት፣ ወራጅ ውኃ ለጠጡባት፣ የገብስ ቆሎ ለበሉባት፣ መልካም አየር ላገኙባት ሀገራቸው ዋጋ ከፍለዋል፡፡
ጌቶቻቸውን ይዘው ዳገቱን ወጥተዋል፣ ቆልቁለቱን ወርደዋል፡፡ በሜዳው ሽምጥ ጋልበዋል፡፡ በሸንተረሮቹ እና በጋራዎቹ ተመላልሰዋል፡፡ በእልህ እና በቁጣ ሽምጥ ጋልበው ከጠላት ሠፈር ገብተዋል፡፡ ጠላትን እየረገጡ ለጌቶቻቸው ሰይፍና ጎራዴ አመቻችተዋል፡፡ ለጦር አስጥተዋል፡፡
እንደ ጌቶቻቸው ሁሉ ለተከበረች ሀገር ደማቸውን አፍስሰዋል፡፡ አጥንታቸውን ከስክሰዋል፡፡ ነፍሳቸውን ሰጥተዋል፡፡ እስከ መጨረሻው ድረስ ታምነዋል፡፡ እስከ መቃብር ድረስ ጸንተዋል፡፡ ፈረስ እና ፈረሰኞች አብረው ጠላትን ድል መትተዋል፡፡ ፈረስና ፈረሰኞች ጸንተው ሀገር አጽንተዋል፡፡ ፈረስና ፈረሰኞች ተማምነው ወራሪን ደምስሰዋል፡፡ ትውልድ የሚኮራበት፣ ሀገር የምትመካበት፣ ከዓለሙ ሁሉ ላቅ ብላ የምትታይበት የማይጠፋ ታሪክ ጽፈዋል፡፡ በወርቅ ቀለም ላይ አቅልመዋል፡፡ በማያረጅ ብራና ላይ አርቅቀዋል፡፡ ለዚያም ይመስላል፡-
“ኧረግ አጅሬ አለው መሐላ
ፈረሱ ላይዝል መውጉያው ላይላላ” ተብሎ የተገጠመው፡፡ ፈረስ እና ፈረሰኞች የተማመኑት በደስታ ጊዜ አይደለም፡፡ ይልቅስ ጦር በሚወረወርበት፣ ጎራዴ በሚፈልቅበት፣ ሰይፍ በሚያበራበት፣ ሞትና መቁሰል በበረከተበት በጦር ሜዳ ነው እንጂ፡፡ በዚያ ሥፍራ ተማምለው በመሐላ አጽንተዋል፡፡ ፈረስ ያደርሳል፡፡ ጀግና ጠላቱን ይደመስሳል፡፡ ፈረስ ያደርሳል ፈረሰኛ ጠላቱን ከድንበር ማዶ ይመልሳል፡፡ ፈረስ ያደርሳል ፈረሰኛ ጠላቱን አፈር ያለብሳል፡፡ እንዲህ ነው የጸኑት፡፡ እንዲህ ነው ሀገር ያቆሙት፡፡ እንዲህ ነው ታሪክ የጻፉት፡፡ እንዲህ ነው ቃል ኪዳን የጠበቁት፡፡ እንዲህ ነው ሉዓላዊነትን ያስከበሩት፡፡ እንዲህ ነው መሐላን ያከበሩት፡፡ እንዲህ ነው አደራ የሰጡት፡ ሀገር ያስረከቡት፡፡ ነጻነት ያወረሱት፡፡ አንድነትን ያስከበሩት፡፡ ሠንደቅ ዓላማን በክብር የሰቀሉት፡፡
ይሄን ያደረጉ ደግሞ ይከበራሉ፡፡ ይዘከራሉ፡፡ እነርሱ በሚዘከሩበት ታላቅ በዓልም ታላቅ ታሪክ ይነገርበታል፤ የጥንቱ ባሕል ይገለጥበታል፡፡ ለነጻነት የተከፈለ መስዋዕትነት ይዘከርበታል፤ ለሉዓላዊነት የተከፈለ ዋጋ ይታወስበታል፡፡ የአበው እና የእመው ሥርዓት ይጠበቅበታል፡፡ የአገው ፈረሰኞች በዓል ታሪክ ሠሪ ፈረሰኞች፣ የሀገር ክብር ጠባቂዎች ከፍ የሚሉበት ነው፡፡ በዚህ በዓል ፈረስ እና ፈረሰኛ ይከበራል፡፡ ባሕል እና ማንነት ይነገራል፡፡ ታሪክ እና ሃይማኖት ይዘከራል፡፡
ጀግኖች በጀግንነት ስለ ሀገራቸው ነጻነት ተዋድቀዋል፡፡ ፈረሶች ጌቶቻቸውን ይዘው ወደ ጦር ሜዳ ገስግሰዋል፡፡ እንደ አርበኞች ሁሉ ተቆጥተው በጠላት ሰፈር ተመላልሰዋል፡፡ ጠላትን ለግዳይ እያዘጋጁ ለጌቶቻቸው ሰጥተዋል፡፡ ጌቶቻቸው የጠላት ጦር እንዳያርፍባቸው አድርገዋልና ይከበራሉ፡፡
የአገው ፈረሰኞች ማኅበር አለቃ አለቃ ጥላዬ አየነው ፈረሶች እና ፈረሰኞች በዓድዋ ዘምተዋል፡፡ ከእነርሱ ጋርም ፈረሰኛው ቅዱስ ጊዮርጊስ አብሯቸው ዘምቷል፡፡ ኀይል ኾኗቸዋል፡፡ ፈረሰች እና ፈረሰኞች በጦርነቱ ደማቸውን አፍስሰዋል፡፡ አጥንታቸውን ከስክሰዋል፡፡ ሕይወታቸውንም ሰጥተዋል ይላሉ፡፡ በዓድዋ ጦርነት ቅዱስ ጊዮርጊስ አባቶቻችን እንደረዳቸው ታሪክ ሲነገር ኖሯል፡፡ አባቶቻችንም ይሄን አቆይተውናል ነው የሚሉት፡፡ ታዲያ ይህ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ኀይል ያለው ጉዳይ የአገው ፈረሰኞችን በዓል የሰጠ ነው፡፡
አበው ከድል መልስ የፈረስ፣ የፈረሰኞች እና የቅዱሰ ጊዮርጊስ ውለታ ምን ይሁን? ብለው መከሩ፡፡ እንግዲያውስ ስማቸው የሚታወስበት፣ ክብራቸው የሚወሳበት የፈረስ ማኅበር ብለን ማኅበር እንጠጣ ብለው ጀመሩ ይላሉ አለቃ የጥንት አመሠራረቱን ሲናገሩ፡፡ ቀኑም የጊዮርጊስ ነው፡፡ በማኀበሩም የተጣላን ያስታርቃሉ፣ ሰላምን ያነግሳሉ፣ ፍቅርን ያጸናሉ፡፡ የፈረሰኞች ማኅበር ፍቅር የተመሠረተበት ነው፡፡ በፈረሰኞች ማኅበር ውስጥ ፍቅር አለ፡፡ ሌባ ይወገዛል፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተገዝቶ ከጥፋቱ ይመለሳል ይላሉ አለቃ፡፡
በፈረሰኞች ማኅበር ይቅርባይነት፣ አንድነት፣ ፍቅር እና ሰላም አለ ነው የሚሉት፡፡ በእነዚያ ጀግኖች እና አርቆ አሳቢዎች የተጀመረው ያ ማኅበር ልጆች እያከበሩት፤ በሥርዓቱ እና በወጉ እየተገዙለት በዝቷል፡፡ ሰፍቷል፡፡ የቀደመው ሥርዓት እና ሕግ ይፈጸምበታል፡፡ ሰዎች ይታረቁበታል፡፡ ፍቅር ይጸናበታል ነው የሚሉት፡፡ በአገው ፈረሰኞች ተመክሮ ከተጣላው ሰው ጋር አልታረቅ ያለ ቢኖር ከማኅበር ይገለላል፡፡ ታቦት አያጅብም፡፡ ቢሞት ፈረስ አይጫንለትም፡፡ ይሄም ስለሚኾን ሕጉን ያከብራል፡፡ አድርግ የተባለውን ያደርጋል፡፡ ጠንካራውን እና ከአባቶች የቆየውን ሥርዓት እና ሕግ ሕዝቡም ይወደዋል፡፡ በሕግ እና በሥርዓቱም ይመራል ነው የሚሉት አለቃ፡፡
የቀደሙ አባቶች ኢትዮጵያ በቅኝ ገዢዎች እንዳትገዛ አድርገው በነጻነት ሰጥተውናል፡፡ እኛም ከእነርሱ ይሄን መማር አለብን ይላሉ፡፡ የሀገር ፈረሰኞች ማኅበር ኢትዮጵያን የሚነካ ባለ ጊዜ ቀድሞ ይነሳል፡፡ እንደ አባቶች ሁሉ ለሀገር ክብር እና ፍቅር ይቆማል ነው የሚሉት፡፡ ትውልዱ ከአገው ፈረሰኞች ማኅበር ባሕል እና ታሪክ መጠበቅን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አንድነትን መማር አለበትም ይላሉ፡፡
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአገው ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ አሳየ ፈረስ እና የአገው ሕዝብ ቁርኝነታቸው የላቀ ነው ይላሉ፡፡ ፈረስ ለማኅበረሰቡ ክብሩ እና ጌጡ ነው፡፡ ፈረስ ለአገው ሕዝብ ልዩ ምልክቱ ነው ይላሉ፡፡ ዓመታዊ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት፣ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች፣ የሰርግ ሥርዓቶች፣ የእርሻ፣ የትራንስፖርት፣ የውቂያ እና ሌሎችን ክዋኔዎች በፈረስ ይፈጽማል ነው የሚሉት፡፡
ስለ አገው ፈረሰኞች ማኅበር አመሠራረት ሲናገሩ “አርበኞች ወራሪውን የጣሊያን ጦር ድል አድርገው ሲመለሱ፣ የተሰውትን ጀግኖች እና የፈረሶቻቸውን ውለታ ለማስታወስ “የዓለም ማኅበር” በሚል በአገው ምድር ደረጃ የፈረሰኛ ማኅበር አቋቋሙ፡፡ ከጦርነቱ መልስ ጀምሮ ማኅበር እንዲጠጣ ተደረገ፡፡ በማኅበሩም የተጣላን ያስታርቃሉ፣ የተቀማን ያስመልሳሉ፣ የሞተን ይቀብራሉ፣ ሰርግ ያጅባሉ፣ ሌሎች ማኅበራዊ ክዋኔዎችን ይፈጽማሉ” ይላሉ፡፡ ይህ ታሪክን መሠረት አድርጎ የተመሠረተው፣ የሕዝብ እሴትን የሚያጎላው ማኅበር በአበው አቀባይነት፣ በልጆች ተቀባይነት ታሪኩ ተጠብቆ፣ ለልጅ ልጅ እየተነገረ ዓመታትን አለፈ፡፡ ዛሬ ላይም ደረሰ፡፡
ከአገው ምድር የተገኙ አርበኞች እና ጌቶቻቸውን በታማኝነት የሚያገለግሉ ፈረሶች በኢትዮጵያ የነጻነት ተጋድሎ ታላቅ አሻራ አስቀምጠዋል፡፡ ከአራቱም ማዕዘን ከተነሱ ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት ጠላትን ድል መትተው ኢትዮጵያን በነጻነት አጽንተዋል፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋን ሠንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ሠቅለዋል፡፡ ጀግኖች ዓድዋን የመሰለ የጀግንነት ታሪክ ጽፈዋል፡፡ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማሕተም፤ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው፡፡ ዓድዋ የታላቅ ሕዝቦች ታላቅ ድል ነው ይላሉ፡፡
እንደ ምሁሩ ገለጻ የኢትዮጵያ ጀግና ሠራዊት በሺህዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን በባዶ እግሩ እና በፈረስ ተጉዞ በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነውን የጣሊያን ወራሪ ጦር የካቲት 23 ድል መትቶታል፡፡ በዚህ አውደ ውጊያ የአገው ፈረሰኞችም ተሳትፈዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ገበሬ ሠራዊት ጋር ተጣምረው እና ተዋሕደው ፈረሶቻቸው ላይ ተቀምጠው አያሌ ጀግንነቶችን ፈጽመዋል፡፡ የጋሻቸውን እምብርት መሬት ላይ እያጠቀሱ፣ ጐራዴያቸውን በአየር እየቀዘፉ፣ በተቆጣ እና በቆረጠ መንፈሥ በጀግንነት ተዋግተዋል፡፡ ደማቸውን አፍስሰዋል፤ አጥንታቸውን ከስክሰዋል፡፡
ጣሊያን ከዓድዋ ሽንፈቷ በኋላ ኢትዮጵያን ለመውረር ዳግም በመጣችበት ጊዜም የአገው ፈረሰኞች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት ጸንተው ጠላትን አንበርክከዋል፡፡ የዚያኔው መጓጓዣ ፈረስ ነበርና በፈረስ ስንቅ እና ትጥቅ ጭነዋል፡፡ በፈረስ ተጉዘዋል፡፡ የጠላት ቅስም የተሰበረው በፈረስ የውጊያ ስልት ነበር ይላሉ ምሁሩ፡፡ ፈረሰኞች ጠላትን የገጠሙት በፈረስ ተፈናጠው ፣ በጎራዴ፣ በጦር፣ በጋሻ እና በውጅግራ መሳሪያዎች ነበር፡፡ በዚህ አውደ ዉጊያ አርበኞች እና ፈረሶቻቸው ለኢትዮጵያ ነጻነት ዋጋ ከፍለዋል፡፡ በደም የተቀለመ ታሪክ ጽፈዋል ነው የሚሉት፡፡
የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ሲቋቋም ዓላማ አድርጎ የተነሳው ለሀገር ነጻነት ፈረስ እና ፈረሰኞች ያደረጉትን አስተዋጽኦ ከመዘከር ባሻገር አያሌ ተግባራት ለመፈጸም ነው ይላሉ፡፡ የማኅበሩ አባላት ሲጣሉ ወደ መደበኛ የፍትሕ አካላት ሳይሄዱ ችግራቸው በማኅበሩ ይፈታል፡፡ የማኅበሩ አባላትም ባይኾኑ እንኳን ሀብት እና ንብረት የተሰረቀባቸው ካሉ ያስመልሳል፡፡ የተቸገሩትን ይረዳል ነው የሚሉት፡፡
የአገው ሕዝብ ለፈረስ ካለው ክብር የተነሳ በበዓልም ኾነ በአዘቦት ለፈረሱ ለኮ፣ ልጓም ፋርኔሳ፣ ኮርቻ ፣ወዴላ እምቢያ ጉስም፣ መቀነቻ፣ ምቹ ግላስ ያጠልቃል፡፡ ፈረሰኛውም ሰውነቱን ታጥቦ ሳሪያን ኮት፣ ባተሁለት ወይም ወንጨሬ፣ ሎፊሳ ከላይ ደርቦ በወገቡ ጀበርና በግራ እጁ ጋሻ በቀኝ እጁ ዘንግ ይዞ ይጋልባል፡፡ በበዓሉ ወቅት ሁሉም ፈረሱን አስጊጦ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ይዞ በታላቅ ክብር ይታያል ይላሉ፡፡
በበዓሉ ወቅት ፈረሰኞች በአለቃቸው እየተመሩ በኅብረት በጥሩንባ፣ በአይሞሎ ዜማ፣ ፈረሱን እና ፈረሰኞችን በሚያሞግስ ቀረርቶና ሽለላ በመታጀብ ደገላንሳን ያሳያሉ፡፡ ሽምጥ በመጋለብ የፈረሱን ጉልበትም ኾነ የእነርሱን ምርጥ ጋላቢነትንም ያሳያሉ፡፡ በጉግስ አባሮ ጋሻ የሚመታበት እና በአርበኝነት ትግሉ ጠላትን እንዴት እንዳሳደደ በሚያጠይቅ መንገድ የፈረስ ውድድር ያካሂዳሉ፡፡ ይህ ትዕይንት ከፈረሱ እና ከፈረሰኛው ዓይን የሚስብ አለባበስ እና አጊያጊያጥ ጋር ሲዳመር አጀብ ያሰኛል ነው የሚሉት፡፡
ምህሩ የአሁኑ ትውልድ ከአገው ፈረሰኞች ማኅበር ግጭቶችን በዘላቂነት መፍታትን መማር አለበት ይላሉ፡፡ በፈረሰኛ ማኅበር አባላት መካከል ግጭቶች ሲያጋጥሙ በመሠረተ ቀበሌ ቀርበው ይታረቃሉ፡፡ ካልታረቁ በቀጣና ጉዳዩ ቀርቦ ይታረቃሉ፡፡ አሁንም ካልታረቁ በወረዳ የፈረሰኛ ማኅበር ዘንድ ይቀርቡና ይታረቃሉ፡፡ በዚህም ካልኾ በዞን የፈረሰኛ ማኅበር ዘንድ ይቀርባሉ፡፡ በዚህም ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ተነጋግረው ይታረቃሉ ይላሉ፡፡ የግጭት አፈታት መንገዱን የዚህ ዘመን ትውልድ ሊማርበት ይገባል ነው የሚሉት፡፡
የእርቅ ሥርዓት ሲፈጸም ለምስክር የሚቀርቡት ሰዎች “ሚካኤል አሳሪ፣ ጊዮርጊስ አባራሪ ይሁንብኝ” ብለው ሀሰት ላለመመስከር መሐላ ፈጽመው ይመሰክራሉ፡፡ ውሸት አይነገርበትምና እርቁ የዕውነት፣ በዕውነት ስለ ዕውነት ነው፡፡ ጸንቶም ይቀራል፡፡
ደስታን እና ሐዘንን መጋራትም ከፈረሰኞች ማኅበር ትምህርት የሚወሰድበት ነው ይላሉ፡፡ የፈረሰኞች ማኅበር በደስታም በሀዘንም አይለያዩም፡፡ የአንደኛው ደስታ የሌላኛው ነው፡፡ የአንደኛው ሀዘንም የሌላኛው ሀዘን ነው፡፡
ገንዘብ እና ቁሳቁስ መዋዋስ መልካም ልምድም በእነርሱ ዘንድ አለ፡፡ የአገው ፈረሰኞች ማኅበር አባላት ገንዘብ እና ቁሳቁስ መዋዋስ የተለመደ ነው፡፡ በመካከላቸው መካካድ አይታሰብም፡፡ ምክንያቱም የፈረስ ጌታ የኾነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያየናል ብለው ስለሚያምኑ በጊዮርጉስ ስም ዕምነታቸውን ያጸናሉ፡፡ ታማኝ አገልጋይነት፣ ጀግንነት፣ ታዛዥነትን፣ ሥራ ወዳድነትን እና ታታሪነትን መማር አለበት ነው የሚሉት፡፡
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በአገው ፈረሰኞች ጥልቅ ጥናት አድርጎ የአገው ፈረስ በዓል የማይዳሰስ ብሔራዊ ቅርስ ኾኖ እንዲመዘገብ አድርጓል ይላሉ፡፡ የአገው ፈረሰኞች የሚጫዎቷቸው የፈረስ ስፖርት አይነቶችን ለይቶ አጥንቷል፡፡ ዓመታዊ ክብረ በዓላት ከነሙሉ ክብራቸው እንዲከወኑ የገንዘብ እና ሙያዊ ድጋፍ ያደርጋል ነው የሚሉት፡፡ በግቢው ውስጥም ዓለማቀፍ ደረጃ የሚያሟላ የፈረስ ስፖርት ባሕል ማጎልበት የሚያስችል ስታዲየም ለመገንባት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ የፈረስ እርባታ ፕሮጀክትም ሌላው በዘርፉ ላይ የተያዘ ዕቅድ ነው ይላሉ፡፡
እነኾ ጥር 23 ደርሳለች፡፡ በጉጉት የሚጠበቀው በዓል ቀርቧል፡፡ ዐይኖች ሁሉ ፈረስ እና ፈረሰኞችን በእንጅባራ ሰማይ ሥር ለማየት ጓጉተዋል፡፡ ስለ ምን ቢሉ ድንቅ ባሕል ይገለጥበታል፡፡ ድንቅ ታሪክ ይነገርበታል፡፡ ፍቅርና ሰላም ይሰበክበታልና፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!