የአጅባር እና ዴንሳ ድምቀት!

65

ባሕር ዳር: ጥር 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቅዱስ መርቆሬዎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በደብረ ታቦር እና በእስቴ መካነ ኢየሱስ ከተሞች በድምቀት ይከበራል። በዓሉ በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚፈጸም፣ ባሕላዊ ክዋኔዎችም የሚበዙበት ነው። በዓሉ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ታላቅ አስተዋጽኦ አለው። ጎብኝዎች የአማራ ክልልን እንዲናፍቁ ከሚያደርጓቸው በዓላት መካከል አንደኛው የቅዱስ መርቆሬዎስ በዓል ነው።

ይህ በዓል በደብረ ታቦር አጅባር ሜዳ፣ በእስቴ መካነ ኢየሱስ እስቴ ዴንሳ ይደምቃል። በዓሉ ደማቅ እና ድንቅ ነው። በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ጎብኝዎችም በስፋት እንዲገኙ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተዋል ተብሏል። የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ የቅዱስ መርቆሬዎስ በዓል በደብረ ታቦር እና በእስቴ መካነ ኢየሱስ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲኾኑ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

በዓሉ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲከበር እንደሚደረግም ገልጸዋል። በዓሉ ለጎብኝዎች ምቹ እና ሳቢ እንዲኾን ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል። በዓሉ የሃይማኖት፣ የባሕል፣ የታሪክ እና የማንነት መገለጫ ስለኾነ ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ መሸጋገር አለበት ነው ያሉት። ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ለማድረግ ሥራዎችን መከናወናቸውን አስታውቀዋል።

የቅዱስ መርቆሬዎስ በዓል ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባለፈ ታሪካዊ እና ባሕላዊ ክዋኔዎች የሚከወኑበት መኾኑን አንስተዋል። በበዓሉ ላይ የሚከወነው የፈረስ ጉግስ ለበዓሉ ልዩ ድምቀት መኾኑንም ገልጸዋል። በዓሉን ለማክበር የሃይማኖት አባቶች እና ወጣቶች እየሠሩ መኾናቸውንም አንስተዋል።

የቅዱስ መርቆሬዎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ለክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው ብለዋል። የቅዱስ መርቆሬዎስ በዓል ክብሩ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በስፋት እንዲመጡባት ማድረግ ይገባልም ብለዋል። በዓሉን የምጣኔ ሀብት ምንጭ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።

በዓሉ ጎብኝዎችን ሲስብ የምጣኔ ሀብት መነቃቃት ያመጣል ነው ያሉት። የጎብኝዎች እንቅስቃሴ ሳይገደብ በተንቀሳቀሱ ቁጥር የቱሪዝም እንቅስቃሴውም አብሮ ይጨምራል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመርጡለ ማርያም የማርያም አዳራሽ ማለት ነው
Next article“ታሪክ ሠሪ ፈረሰኞች፤ የሀገር ክብር ጠባቂዎች”