
ባሕር ዳር: ጥር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት ከሀገር የወጡ ከ70 በላይ ቅርሶች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ መደረጉን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ገልጿል።
ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ አይነተ ብዙ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ቅርሶች ባለቤት ስትኾን በርካታ ቅርሶቿም በዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ተንቀሳቃሽ ታሪካዊ ቅርሶቿ በተለያዩ ዘመናት ከሀገር እየተዘረፉ ወጥተው በተለያዩ ሀገራት፣ ተቋማት እና ግለሰቦች እጅ ይገኛሉ።
በዓለም ላይ ተሠርቀው ተወስደው የሚገኙ ቅርሶችን ለማስመለስ የሀገር ተቆርቋሪ ምሁራን፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ እና ታዋቂ ሰዎችን ያቀፈ የኢትዮጵያ ቅርሶች አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጥረት አድርጓል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው ባለሥልጣኑ ከተንቀሳቃሽ ቁስ እስከ ታሪካዊ ሥነ ሕንጻዎች የጥበቃ እና የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) ሀሳብ አመንጭነት የሚከናወኑ የብሔራዊ ቅርሶች ዕድሳትን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የቅርሶች ጥበቃ፣ ዕደሳት እና ጥገና እየተደረገ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ከቅርስ ጥበቃ እና ልማት ባሻገር በየዘመናቱ ከሀገር የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ በመንግሥት እና በብሔራዊ ኮሚቴው መሠራቱን ገልጸዋል። በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ በተለያዩ ጊዜያት ከሀገር የወጡ ከ70 በላይ ቅርሶችን ማስመለስ እንደተቻለም ተናግረዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ቅርሶች ከማንነት እና ከታሪካዊ መገለጫነታቸው ባሻገር ለቱሪዝም ኢኮኖሚ ያላቸው ትልቅ ነው ብለዋል። የሀገር ውድ ሀብቶች መኾናቸውንም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!