ከ50 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ።

23

ጎንደር: ጥር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተግባራትን ማስፋት ላይ ያተኮረ ውይይት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል። ውይይቱ በተያዘው በጀት ዓመት ለነዋሪዎች የጤና መድኅን አገልግሎት ተደራሽ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነው።

የከተማ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ ኀላፊ ሰዒድ የሻው እንደገለጹት በተያዘው በጀት ዓመት ከ50 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ እየተሠራ ነው። እስካሁን በተሠራው ሥራ 9 ሺህ አባላትን ማፍራት መቻሉን ተናግረዋል። በመንግሥት በኩልም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች በጀት መድቦ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሠራ ነውም ብለዋል።

በበጀት ዓመቱም ከአገልግሎቱ 101 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 20 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን አቶ ሰዒድ ተናግረዋል። በከተማ አሥተዳደሩ አዲስ አባላትን ለማፍራት የሚያስችል የግንዛቤ ፈጠራን ጨምሮ በተገልጋዮች በኩል የሚነሱ የመድኃኒት አቅርቦት እና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ አቶ ሰዒድ አስታውቀዋል።

በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ክሽን ወልዴ በበጀት ዓመቱ በክልሉ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልፀዋል። በማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ተገልጋዮች በኩል የሚነሳውን የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤቶች አገልግሎት እንዲሰጡ በማቀድ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።

ለአብነትም በደሴ ከተማ የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤቶች አገልግሎት መጀመራቸውን አስታውቀው ይህን ተሞክሮ በጎንደር እና ሌሎችም ከተሞች ለማስፋት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

በጎንደር ከተማ የጤና መድኅን አገልግሎትን ተደራሽነትን በማስፋት እቅዱን ለማሳካት እስከ የካቲት 5/2017 ዓ.ም በንቅናቄ እንደሚሠራም ተገልጿል።

ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“አሚኮ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ጉልህ አበርክቶ ያለው የሚዲያ ተቋም ነው” የሚዲያ ባለሙያዎች
Next articleአሚኮ ምቹ ባልኾኑ ሁኔታዎች ውስጥ እያለፈ ውጤታማ ሥራን እየሠራ ያለ አንጋፋ ተቋም መኾኑን የሚዲያ ባለሙያዎች ተናገሩ።