
ባሕርዳር፡ጥር 20/2017 ዓ.ም(አሚኮ) 85ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታውቋል። በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከዚህ ቀደም የተከበሩ የልደት፣ የከተራ እና የጥምቀት በዓላት ያለምንም የጸጥታ ችግር ተከብረው መዋላቸው ተመላክቷል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር እሱባለው መኮነን ከአሁን ቀደም የተከበሩ በዓላት በሰላም መጠናቀቃቸው ሕዝቡ ሰላም ወዳድ እና ሕግ አክባሪ መኾኑን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።
በዓላት በሰላም ተከብረው እንዲውሉ የጸጥታ መዋቅሩ የተቀናጀ ሥራ እና የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል። ሰላም በፖሊስ አካል ብቻ የሚመጣ ባለመኾኑ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ማኅበረሰቡ ተደራጅቶ ከጸጥታ አካላት ጎን እንዲቆም ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት፡፡ የአገው ፈረሰኞች በዓልም በሰላም ተከብሮ እንዲውል የፖሊስ መዋቅሩ ስምሪት መውሰዱን ገልጸዋል፡፡
በበዓሉ እንግዶች ያለስጋት በሰላም እንዲያክብሩ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ መሠራቱን የተናገሩት ኀላፊው እንግዶች በዓሉን ለማክበር የሚያሰጋቸው ነገር እንደሌለም ተናግረዋል። የሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር እንግዶች የአገው ፈረሰኞች በዓልን በእንጅባራ ተገኝተው እንዲያከብሩም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ማኅበረሰቡ አጠራጣሪ እና የተለየ ነገር ሲመለከት ለጸጥታ አካላት መረጃ እንዲሰጥም አሳስበዋል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አንዱዓለም አበሻ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የሚሊሻ ኀይሉ የተወጣው ኀላፊነት ትልቅ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት በተከበሩ በዓላት ሰላምን የሚያውኩ ነገሮች አለመከሰታቸውን አስታውሰዋል። በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ ጠንካራ ስምሪት መሰጠቱንም ገልጸዋል።
ጥር 23/2017 ዓ.ም እንጅባራ ከተማ ላይ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበረውን 85ኛ የአገው ፈረሰኞች በዓል በሰላም እንዲከበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በመኾን ማጠናቀቃቸውንም አስታውቀዋል። ማኅበረሰቡ ባለፉት በዓላት ያሳየውን መተባበር እና ቅንጅት ለጥር 23 በዓልም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሰላም እና ድኅንት መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው ቢሻው ያለፉት በዓላት በሰላም ተከብረው እንዲጠናቀቁ መንግሥት ኀላፊነቱን በሚገባ መወጣቱን ገልጸዋል። የጸጥታ ኀይሉ በሠራው ጠንካራ የስምሪት እና የክትትል ሥራ ሕዝቡ በዓላትን በሰላም ማሳለፉን ተናግረዋል። ለዚሕም የሕዝቡ ሚና ከፍ ያለ እንደነበር ነው ያነሱት።
ጥር 23 የሚከበረው 85ኛ የአገው ፈረሰኞች በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲውል አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቅቀዋል ብለዋል፡፡ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ በየደረጃው ካሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል። በዓሉን ምክንያት በማድረግ በአግልግሎት ዘርፍ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ጠንካራ ስምሪት ተሰጥቶ ክትትል እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
የእንጅባራ እና አካባቢው ማኅበረሰብም በዓሉን ለማክበር ወደ እንጅባራ ከተማ ለሚመጡ እንግዶች በቆዬው የእንግዳ አቀባበል ባሕል እንግዶችን እንዲቀበልም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ሰሎሞን ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!