
የአማራ ክልል ደራሲያን ማኅበር አባላት ዛሬ በባሕርዳር ደም ባንክ ደም ለግሰዋል፡፡
የማኅበሩ አባል ወይዘሮ መቅደስ ዐቢይ በደም እጦት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል፡፡ “ገንዘብ ይዘው እንኳን ለታማሚዎች ደም ለማግኘት ሰዎች ሲቸገሩ አይቻለሁ” ያሉት የማኅበሩ አባል ደም መለገስ የሚችል ሁሉም ሰው በዚህ በጎ ተግባር መሳተፍ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ እስከ አሁን ደም ያልለገሱ ሰዎች በመለገስ የሚገኘውን እርካታ ማጣጣም እንዳለባቸውም ወይዘሮ መቅደስ አስገንዝበዋል፡፡
ሌላው በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሽ አቶ አዲሱ አበባው ደግሞ “በአሁኑ ጊዜ በኮሮና ወረረሽኝ ምክንያት በክልሉ የደም እጥረት አጋጥሟል” መባሉን ሰምተው ለመጀመሪያ ጊዜ ደም መለገሳቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በሌላ ጊዜም እንደሚለግሱ ቃል ገብተዋል፡፡
የአማራ ክልል ደራሲያን ማኅበር ፕሬዝዳንት ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን በበኩላቸው ማኅበሩ ከሕዝብ ጎን መቆሙን ለማሳየት አባላቱ ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል፤የሚችሉ ሁሉ ደም እንዲለግሱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የባሕር ዳር ደም ባንክ ባለሙያ ሲስተር ገነት አስፋው ለአብመድ እንደገለጹት ደግሞ ደም ባንኩ በያዝነው ዓመት 12 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ አቅዶ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 16 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ግን የደም ለጋሾች ቁጥር 80 በመቶ መቀነሱን ገልጸዋል፡፡ ማኅበረሰቡም ይህንን በመረዳት በወሊድ፣ በካንሰር ህመም እና በልዩ ልዩ አደጋዎች ምክንያት ደም ለሚያስፈልጋቸው በመለገስ ሕይወታቸውን እንዲታደጉላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በደም ልገሳ ጊዜ ለለጋሾች ጥንቃቄ እንደሚደረግላቸውም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሺባባው