ጦርነትን፣ ስደትን እና ችግርን የሚያባብሱ አጀንዳዎች በየትኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የላቸውም።

22

ሁመራ: ጥር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሰቲት ሁመራ ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከወጣቶች ጋር ውይይት አካሂዷል። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኀላፊ ገብረዮሐንስ የሽነህ ዞኑ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል። ቅድሚ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ሁሉም የድርሻውን እያበረከተ መኾኑንም አንስተዋል።

ከችግሮቻችን በላይ የወሰን እና የማንነት ጉዳይ ትልቁ ጉዳያችን ነው ያሉት ደግሞ የሰቲት ሁመራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ዓለሙ አየነው ናቸው። ሰላምን ለማጽናት እና ማንነትን ለማረጋገጥ ከላይ እስከ ታች ወጣቱን የመሰብሰብ፣ የማወያየት፣ የማደራጀት እና ጥያቄዎቹን የመመለስ ኀላፊነቱ የመሪዎች ድርሻ ነውም ብለዋል።

ሁላችንም አንድ የሚያደርገን ጉዳይ አማራነታችን ነው ያሉት አቶ ዓለሙ ስለ አንድነታችን እና ማንነታችን ያለመታከት መሥራት የሁላችን ድርሻ ነው ብለዋል። ጦርነትን፣ ስደትን እና ችግርን የሚያባብሱ አጀንዳዎች በየትኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የሌላቸው መኾኑንም አቶ ዓለሙ ጠቅሰዋል።

ከንቲባው የዞኑን ሰላም እና ጸጥታ ለማረጋገጥ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት የጸጥታ መዋቅሩን አጠናክረናል ብለዋል። የሥራ ዕድልን በማስፋፋት እና ወጣቱን የሥራ ባለቤት በማድረግ ተጠቃሚነቱን እያረጋገጥን ነው ያሉት ደግሞ በአማራ ክልል የሰቲት ሁመራ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እንኳየነህ ሙሉ ናቸው።

ሰላም እና ደኅንነትን ከመጠበቅ ጎን ለጎን ወጣቱን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የዞኑን እና የቀጣናውን ሰላም ማስጠበቅ የሚቻለው ወጣቱን ማሥተባበር እና ማሳተፍ ሲቻል እንደኾነም ወጣቶቹ ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ሕዝባዊ የሰላም ውይይት ተካሄደ።
Next articleበራያ ቆቦ ሕዝባዊ የሰላም ውይይት ተካሄደ።