ደማቁ እና ተናፋቂው የአገው ፈረሰኞች በዓል!

23

ባሕር ዳር: ጥር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ፈረሶቹ ጋላቢዎቻቸውን ያውቃሉ፤ ጋላቢዎቹም እንደልጆቻቸው ያሳደጓቸውን እና እንደፈለጉ የሚያሾሯቸውን ፈረሶቻቸውን ያስጌጣሉ። የአገው ፈረሰኞች በዓል ተናፋቂ እና ደማቅ ነው። ፈረሰኞች የሚደምቁበት፣ ያማሩ ፈረሶች የተዋቡ ፈረሰኞችን ይዘው የሚታዩበት 85ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል ደርሷል። ደማቁን በዓል የምታስተናግደው እንጅባራ ከተማም ተዘጋጅታለች።

እንግዳን መቀበል የሚያውቁት ነዋሪዎቿ አዲናስ እያሉ ይቀበላሉ። ባሕል፣ ታሪክ፣ ማንነት እሴት የሚገለጽበት በዓል በጉጉት እየተጠበቀ ነው። ጥር 23 ተናፍቃለች። በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ሊቀመንበር አለቃ ጥላዬ አየነው ነግረውናል፡፡

ይህ አርበኝነት፣ ነጻነት፣ አሸናፊነት፣ የሀገር ፍቅር እና አንድነት የሚንጸባረቅበት በዓል የቀደሙ አርበኞች ይታሰቡበታል። ይዘከርበታል። ታሪክ ይነገርበታል። ለትውልድም ይተላለፍበታል። በዓሉ የአርበኞችን፣ የፈረሰኞችን እና አብሮ የዘመተውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦትን ውለታ ለማስታወስ በሚል የተጀመረ እንደኾነ ሊቀመንበሩ ነግረውናል።

ከዛም ትውልድ ሲቀባበለው ቆይቶ ተረካቢው የአሁኑ ትውልድም እያስቀጠለው መኾኑን ገልጸዋል። ፈረሶቹ በዚህ በዓል ላይ በልዩ ሁኔታ መዘጋጀታቸውን የሚናገሩት አለቃ ጥላዬ የሰላምታ አሰጣጥ፣ የድንግል ዓሳ ትርዒት፣ የፈረስ ስግሪያ፣ የፈረስ ጉግስ እና ሽርጥ በሴቶችም በወንዶችም የሚቀርብ ልዩ ትዕይንት ይካሄዳል ነው ያሉት።

የአገው ፈረሰኞች በዓል 62 ሺህ 739 አባላት አሉት። ኢትዮጵያውያን በአጓጊው እና በደማቁ በዓል እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleስለይቅርታ ሕጉ ምን ይላል?
Next articleበደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ሕዝባዊ የሰላም ውይይት ተካሄደ።