ስለይቅርታ ሕጉ ምን ይላል?

39

ባሕር ዳር: ጥር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ይቅርታ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀጽ 229፣ በሀገሪቷ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 28፣ በአማራ ክልል ደግሞ የይቅርታ ጉዳይ የሕግ ማዕቀፍ የተሰጠው አዋጅ ቁጥር 136/1998 እና ይህን ለማስፈጸም የወጣው መመሪያ ቁጥር 30/2010 ላይ ሰፊ የሕግ ማዕቀፋ የተበጀለት ጉዳይ ነው።

ስህተት ሰዋዊ ባህሪ ነው። በዕለት ከዕለት መስተጋብርም ስህተት የሚጠበቅ ክስተት ነው። በዚያም ምክንያት አድማሱን አስፍቶ ወደ ግጭት፣ አለመስማማት እና ከፍ ሲልም ወደ ወንጀል የሚደርስበት አጋጣሚ ይፈጠራል። ይህን ሰዋዊ ባህሪ ለመሻገር እና ለመሻር ይቅርታ ፍቱን መድኃኒት ነው። ይቅርታ ትልቅነት ነው። በሕግም የሚደገፍ ተግባር ነው።

አቶ ንጉሴ ዘገየ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የወንጀል ዐቃቤ ሕግ ናቸው። ይቅርታ አንድ ሰው ለፈጸመው ወንጀል ወይም በደል የተጣለበትን ቅጣት ለመቀነስ እና በዚሁ ምክንያት ያጣቸውን መብቶች እና ጥቅሞች ለማስመለስ በመንግሥት አሥፈጻሚ አካላት የሚወሰድ እርምጃ ነው ይላሉ። በሀገራችን እንደ ባሕልም ይቅርታ አንድ የበደለ አካል ተበዳዩን ያጠፍሁትን ጥፋት ይቅር በለኝ ብሎ በራሱ ተነሳሽነት ጥያቄ የሚያቀርብበት ክንውን ነው ብለዋል።

ወደ መደበኛው የወንጀል ተግባር እና ይቅርታ አሰጣጥ ሥርዓቱ ስንወስደው ደግሞ ይላሉ አቶ ንጉሴ ዘገየ በተለያየ አጋጣሚ ወንጀል የሠራ አካል ተገቢው ምርመራ ተደርጎበት እና የጥፍተኝነት ውሳኔ ከተላለፈበት በኋላ ውሳኔው ወይም የቅጣት ዘመኑ ከማለቁ በፊት በይቅርታ ነጻ የሚኾንበትን መንገድ የሚመለከት ነው።

የይቅርታ አሰጣጥ ሥርዓቱ ሂደት አለው የሚሉት ዐቃቤ ሕጉ ይቅርታ ጠያቂው ለሚመለከተው የመንግሥት አካል የይቅርታ ጥያቄ ያስገባል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው እና በየደረጃው ያሉ የይቅርታ አደረጃጀት ኮሚቴዎችም የወንጀል ፈጻሚውን የይቅርታ ጥያቄ በሚገባ ያጤኑታል ነው ያሉት።

ይቅርታ ከመደረጉ በፊት መጣራት ያለባቸው ጉዳዮች ሂደታቸውን ተከትለው እንደሚጓዙም ያነሳሉ። በኮሚቴዎች ሲታይ የቆየው ጉዳይም እንደገና በክልል የይቅርታ መርማሪ ቦርድ አማካኝነት የግለሰቡ ጉዳይ ለይቅርታ ያበቃዋል ወይስ አያበቃውም የሚለው ነገርም ይታያል ብለዋል።

የመርማሪ ቦርዱ ውሳኔውን ለመሥተዳደር ምክር ቤቱ የደረሰበትን ውጤት ያደርስ እና የክልል መሥተዳድር ምክር ቤቱ ጉዳዩን ካየ በኋላ ይቅርታ እንዲሰጠው ይኾናል ሲሉ እንደ ክልል በሥራ ላይ ያለውን አካሄድ አንስተዋል። በፌደራል ደረጃም ቢኾን አካሄዱ ተመሳሳይ ይዘት ያለው እንደኾነ አንስተዋል። በፌደራል ፍርድ ቤቶች በኩል የቀረበው የወንጀለኛ ጉዳይ ለፌደራል የይቅርታ መርማሪ ቦርድ ቀርቦ ጥያቄውን በውል ካጣራ በኋላ ውሳኔውን ለርእሰ ብሔሩ ይቀርባል ይላሉ።

በፌደራል ደረጃ ይቅርታ የሚሰጡት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79 መሠረት ርእሰ ብሔሩ ናቸው ነው ያሉት። ስለዚህ ይቅርታው የመጨረሻ የሚሰጠው በክልል ደረጃ በክልል መሥተዳድር ምክር ቤቱ ሲኾን በፌደራል ደረጃ ደግሞ በርእሰ ብሔሩ እንደኾነ ተናግረዋል።

የይቅርታ ዓላማው በዋናነት የሕዝብን፣ የመንግሥትን እና የታራሚዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል ታራሚዎች በፈጸሙት ጥፋት ተጸጽተው እና ታርመው አምራች እና ሕግ አክባሪ ዜጋ እንዲኾኑ ማስቻል እንደኾነ የአማራ ክልል የይቅርታ አሰጣጥ እና አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 30/2010 ዓ.ም የወጣው መመሪያ ያስገነዝባልም ብለዋል።

አንድ ታራሚ 20 ዓመት የተፈረደበት ቢኾን ይህን ሁሉ ጊዜ በማረሚያ ቤት ከሚያሳልፍ ሕግ የሚያዘውን ሁሉ ያሟላ ታራሚ ወደ ሕዝቡ ቢቀላቀል ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው ይላሉ አቶ ንጉሴ ዘገየ። ይህ የሚኾነው ግን በየደረጃው ያሉ የይቅርታ መርማሪዎች ተገቢነቱን ካረጋገጡ ብቻ እንደኮነም ጠቁመዋል።

የሕግ ባለሙያው አንድን የሕግ ታራሚ ለይቅርታ የሚያበቁ ጉዳዮች ብለው ያነሷቸው መመሪያ 30/2010 መሠረት የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ሰው ወንድ ከኾነ እና 12 ዓመታት ከታሰረ፤ ሴት ኾና ደግሞ 10 ዓመታት ከታሰረች በዃላ ይቅርታውን ለመጠየቅ ቅድመ ኹኔታውን ያሟሉ እንደኾነ በሕጉ ተቀምጧል ብለዋል።

ሌላው ከዕድሜ ልክ እስረኞች ውጭ ቅጣት የተጣለባቸው ፍርደኞች ደግሞ አጠቃላይ ከተፈረደባቸው ውስጥ አንድ ሦስተኛውን ከታረሙ ይቅርታ ለመጠየቅ ቅድመ ኹኔታውን እንደሚያሟሉ ጠቁመዋል። በሐሰተኛ ማስረጃ የተፈረደባቸው ግለሰቦች ከጊዜ በኋላ ወንጀሉን እንዳልፈጸሙ ተረጋግጦ ሲገኝ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ የይቅርታው ተጠቃሚ ይኾናሉ።

የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ ይህን ጉዳይ ስለማይመልሰውም የይቅርታ መመሪያው ይህን መፍታቱ መልካም ያደርገዋል ይላሉ። እንደ ሕግ ባለሙያው ገለጻ ፍርደኞች ባይጠይቁም እንኳ መንግሥት በራሱ ተነሳሽነት ይቅርታ የሚያደርግባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉም አንስተዋል። ለአብነት ያነሱት መንግሥት የግለሰቦቹ በይቅርታ መፈታት ለሕዝብ ጥቅም አሰፈላጊ ናቸው ብሎ የሚያምንባቸው ከኾነ ነው ብለዋል።

ከዕድሜ ጋር በተያያዘም ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች ያሉ እና ከተፈረደባቸው ውስጥ ወንዶች አንድ አራተኛውን ሴቶች ደግሞ አንድ አምስተኛውን እርምት ከወሰዱ የይቅርታው ተጠቃሚ ይኾናሉ ብለዋል። ዕድሜያቸው 60 ዓመት የኾናቸው ወንዶች ከተፈረደባቸው ውስጥ 10 ዓመት ከታረሙ፣ ሴቶች ደግሞ 55 ዓመት ኾኗቸው ስምንት ዓመት እርምት ከወሰዱ ይቅርታ ይደረግላቸዋል ይላል ሕጉ ነው ያሉት። ይሁን እና የባህሪ ለውጥ ማምጣት ግን አንድ ቅድመ ኹኔታ ነውም ብለዋል።

ነፍሰ ጡር ሴቶች ከተወሰነባቸው ውስጥ አንድ አምስተኛውን ከታረሙ እና የባህሪ ለውጥ ካመጡ የይቅርታ ተጠቃሚ እንደሚኾኑም ገልጸዋል። አንድ የአዕምሮ በሽተኛ ኾኖ ከሚያስቸግር እና ከሚቆይ ይልቅ መለቀቁ የተሻለ እንደኾነ ከታመነበትም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በይቅርታ ይለቀቃል ነው ያሉት።

በቀላሉ የማይድን የጤና ችግር ያለባቸው ግለሰቦች ከተፈረደባቸው ውስጥ አንድ አራተኛውን ከታረሙ እና የባህሪ ለውጥ ካመጡ የይቅርታው ተጠቃሚ እንደሚኾኑም ዐቃቢ ሕጉ ንጉሴ ዘገየ አስረድተዋል። ይቅርታ ከማይደረግባቸው ወንጀሎች ውስጥ ደግሞ በሀገሪቷ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 28 ላይ የተቀመጡ እንዳሉም አንስተዋል።

ለምሳሌ የዘር ማጥፍት ወንጀል የፈጸመ ሰው፣ ያለ ፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ የወሰደ ሰው፣ ሰውን አስገድዶ የሰወረ፣ ኢ-ሰብዓዊ የድብደባ ወንጀል ሠርቶ የተፈረደበት፣ ከ15 ዓመት በታች ያሉ ህጻናትን አስገድዶ የደፈረ እና የጠለፍ ወንጀል የፈጸመ፣ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የፈጸመ፣ ሐሰተኛ ገንዘብ መሥራት እና ማዘዋወር፣ የሽብርተኝነት ወንጀል የፈጸመ ጥፍተኛ የይቅርታ ተጠቃሚ የማይኾኑ ወንጀለኞች እንደኾኑ በመመሪያው ላይ ተቀምጧል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ ባጋጠመ ብልሽት ምክንያት ከኮሶበር ቻግኒ መስመር የኃይል አቅርቦት ተቋርጧል።
Next articleደማቁ እና ተናፋቂው የአገው ፈረሰኞች በዓል!