ለዘላቂ ሰላም መስፈን ኅብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ፡፡

34

ባሕር ዳር: ጥር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ”ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የኅብረተሰቡ ሚና” በሚል መሪ መልዕክት ኅብረተሰቡን በየክፍለ ከተሞቹ እያወያየ ነው። በውይይቱ የከተማውን ብሎም የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ስለማስፈን፣ ልማት እና መልካም አሥተዳደር ስለሚሰፍንበት ኹኔታ ውይይት ተደርጓል።

የግሽ ዓባይ ክፍለ ከተማ የሕዳሴ ቀበሌ ነዋሪ ሰለሞን ስዩም በከተማው የጸጥታውን ችግር ምክንያት በማድረግ የሚረብሹትን እና ወጣቱ እንዳይረጋጋ የሚፈልጉ አካላት የሚነዙትን አሉባልታ መታገል እንደሚገባ ገልጸዋል። ያጋጠመው የሰላም ችግርም መፈታት ያለበት በውይይት ነው፤ ለዚህም መንግሥት የሰላም ጥሪውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ማኅበረሰቡም ስለሰላሙ መወያየት፣ ዘላቂ መፍትሄ ማፈላለግ አካባቢውን እና ክልሉን መጠበቅም አለበት ነው ያሉት። ጫካ ያሉ ወንድሞችም የጦርነትን መጥፎነት እና ስቃይ ተረድተው ወደ ሰላም መምጣት አለባቸው ብለዋል። የአጼ ቴዎድሮስ ከፍለ ከተማ የአየር ጤና ቀበሌ ነዋሪ መቶ አለቃ አበባው ፈረደ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት መንግሥት ሕዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት፣ በሀገር ደረጃ ምላሽ ማግኘት ያለባቸውን ደግሞ ተመካክሮ መፍታት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ለሰላም የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እና ለድርድር ዋጋ ሰጥቶ መሥራት እንዳለበትም አብራርተዋል። የታጠቁ ኀይሎችም በሰላም ወደ ሰላም እንዳለባቸው ተናግረዋል። ሽማግሌዎችንም በመስማት ከመንግሥት ጋር ለመደራደር እና ሰላም ለማስፈን ዝግጁ መኾን አለባቸው ብለዋል።

በግሽ ዓባይ ክፍለ ከተማ የሰላም በር ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ኡመር ሙሐመድ በግጭቱ ምክንያት ስርቆት እና ረብሻ እንደነበር ገልጾ አሁን የሰላሙ ኹኔታ በመሻሻሉ እፎይታ መገኘቱን ጠቅሷል። ስርቆት እና እገታን ለመከላከል በመመካከር እና ወጣቱን በማደራጀት ሰላሙን መጠበቅ ይገባል ነው ያለው።

ኅብረተሰቡም ችግሮችን ሲያይ ለሚመለከተው አካል መጠቆም እና በድፍረት መናገር አለበት ብሏል፡፡ የግሽ ዓባይ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት እና የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ሀብታሙ አላምረው ለሰላም መስፈን የኅብረተሰቡ ሚናን ወሳኝነት አንስተዋል፡፡

በመወያየት የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ እና ይህንንም አስተዋጽኦውን ማስቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ጫካ ያሉ ወገኖችም የሰላምን አስፈላጊነት ተረድተው ወደ ሰላም መምጣት አለባቸው ነው ያሉት፡፡ መንግሥት ሰላም የማስከበር ኀላፊነቱን ይበልጥ በማጠናከር ያለውን ሰላም አጠናክሮ ሊያስቀጥል እንደሚገባ ከኅብረተሰቡ መነሳቱን ገልጸዋል፡፡

የሰላም እና የልማት ጥያቄዎችንም መመለስ እና ወጣቶችንም አቅርቦ ማወያየት እንደሚገባ ስለመነጋገራቸው ነው የገለጹት። አሁን ለተፈጠረው ኹኔታ የዳረገው የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ጭምር መኾናቸውን በመረዳት የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል እና ልማትን በማፋጠን ለሕዝብ ጥያቄ መልስ ለመስጠት እየተሠራ ነው ብለዋል።

ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀራርበን እየተወያየን በመሥራትም ሰላማችን ዘላቂ እናደርጋለን ነው ያሉት። የተጀመሩ የልማት ሥራዎችም ይጠናቀቃሉ ብለዋል። በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ጊዜው ታከለ የኅብረተሰብ ውይይቱ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ማኅበረሰቡም ሚናውን እንዲወጣ ለማስቻል ነው ብለዋል።

የጥር ወር በዓላት በባሕር ዳር ሲከበሩ ለሰላሙ የሠራው ኅብረተሰቡ መኾኑን ጠቅሰው ሰላሙን ለማዝለቅ ሕዝቡን ባለቤት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ ሕዝቡ በውይይቶች በንቃት ተሳትፎ፣ ለሰላሙ ዘብ እንዲቆም እና ሰላም እንዲሰፍን የሁሉም አስተዋጽኦ እንደሚያስፈልግ ሃሳብ መነሳቱንም ጠቁመዋል፡፡

ግጭት በመፍጠር ችግር እንደማይፈታ፤ ለሰላም፣ ለልማቱ እና ለመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች መንግሥት ምላሽ እንዲሰጥ፤ ማኅበረሰቡም የራሱን ሚና እንዲወጣ ሃሳብ ተነስቷል፡፡

ከተማ አሥተዳደሩም ከሕዝቡ ጋር በመኾን ሰላሙን እንደሚያሰፍን እና ልማቱን እንደሚያስቀጥል ገልጸዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየ844 አባዎራዎች የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት ወጭ በበጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ተሸፍኗል።
Next articleበኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ ባጋጠመ ብልሽት ምክንያት ከኮሶበር ቻግኒ መስመር የኃይል አቅርቦት ተቋርጧል።