የ844 አባዎራዎች የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት ወጭ በበጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ተሸፍኗል።

24

እንጅባራ: ጥር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ2017 በጀት ዓመት በነባር እና በአዲስ ከ261 ሺህ በላይ አባዎራዎችን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል። ከዚህ ውስጥ 23 በመቶ የሚኾኑት በድሃ ድሃ ማዕቀፍ ወጭያቸውን መንግሥት የሚሸፍንላቸው ናቸው ተብሏል።

ከባለፈው ታኅሣሥ ወር ጀምሮ በተሠራው ሥራም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ111ሺህ በላይ አባዎራዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ኾነዋልም ነው የተባለው። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያም በበጀት ዓመቱ የተሠሩ ሥራዎችን እና ያጋጠሙ ችግሮችን ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በእንጅባራ ከተማ ገምግሟል።

በግምገማ መድረኩ የተገኙት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ የጤና አገልግሎት ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መኾኑን ተናግረዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በነባር አባላት እድሳት እና አዳዲስ አባላትን በማፍራት ረገድ የተመዘገበው ውጤት አበረታች አንደኾነም ገልጸዋል። ከወረዳ ወረዳ እና ከከተማ ከተማ ያለውን የአፈፃፀም ልዩነት ለማቀራረብ የፖለቲካ አመራሩ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት። የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ ኀላፊ አየለ አልማው ባለፈው ዓመት የነበሩ ድክመቶችን ሊያካክስ በሚያስችል ቁጭት ወደ ሥራ በመገባቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዕቅዱን 42 ነጥብ 4 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ 295 በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ለ844 አባዎራዎች ዓመታዊ ክፍያቸውን እንደሸፈኑላቸውም ኀላፊው ገልጸዋል። ከጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የጤና ተቋማትን በሰው ኀይል እና በሕክምና ግብዓቶች የማደራጀት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ኀላፊው አንስተዋል።

በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሁለት ወረዳዎች እና አንድ ከተማ አሥተዳደር እስከ አሁን ድረስ አገልግሎት እንዳልጀመሩ ያነሱት ኀላፊው አገልግሎቱ እንዲጀመር ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። በበጀት ዓመቱ ከአባላት መዋጮ ከ273 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሠብሠብ መታቀዱንም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማጽናት የሁሉም ርብርብ ሊኖር ይገባል።
Next articleለዘላቂ ሰላም መስፈን ኅብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ፡፡