
ባሕር ዳር: ጥር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሥር የሚገኙት የጣና፣ የፋሲሎ እና የዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ”ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የኅብረተሰቡ ሚና” በሚል መሪ መልዕክት ውይይት እያደረጉ ነው።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ እና የጣና ክፍለ ከተማ አወያይ ዘመነ አሰፋ አሁን ላይ በጥምር የጸጥታ ኃይሉ እና በሰላም ወዳዱ ኀብረተሰብ ሰላም ማስፈን ተችሏል ብለዋል። ትልልቅ ሃይማኖታዊ በዓላትን በሰላም ማክበር እንደተቻለም አንስተዋል። በገጠር ቀበሌዎች ሰላምን በማጽናት መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማስቀጠል ተችሏል ነው ያሉት።
አሁንም ሰላም በዘላቂነት እንድሰፍን ማኀበረሰቡ የራሱን ድርሻ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት አቶ ዘመነ መንግሥት ብቻውን ዘላቂ ሰላም ማስፈን አይችልም ብለዋል። ለሰላም የማይመለከተው ኀብረተሰብ የለም። ለሰላም የሚቆጠብ ጉልበት መኖር የለበትም ነው ያሉት። በባሕር ዳር ከተማ የፋሲሎ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ገረመው አባተ ሰላምን ለማጽናት ኀብረተሰቡን ማወያየት እና መግባባት ላይ መድረስ ተገቢ ነው ብለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ አንጻራዊ ሰላም አለ ያሉት አቶ ገረመው በዘላቂነት ለማስቀጠል የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ከኀብረተሰቡ የመፍትሄ ሐሳብ ይፈለጋል ነው ያሉት። ከማኅበረሰቡ የሚነሳው ሃሳብ ሰላምን ለማጽናት ሚናው ከፍተኛ ነውም ብለዋል። በውይይቱ ኀብረተሰቡ ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናት በርብርብ መሥራት እንደሚገባም ተገልጿል።
የጣና ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ብርሃኑ ዓይናለም ብዙ ዋጋ ተከፍሎ የተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲኾን ኀብረተሰቡ የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል። መረጃ ለጸጥታ ኃይሎች በመስጠት፣ አጥፊዎችን በመገሰጽ እና በመጠቆም ረገድ የኀብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ እንደኾነም ተናግረዋል።
ሰላም በጦርነት አይገኝም ያሉት አቶ ብርሃኑ የሰላም ካውንስሉ ሥራውን አጠናክሮ መከወን ይኖርበታል ነው ያሉት። የዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ድግሴ መንግሥት ሰላም ሲኖር ነው መኖር የሚቻለው፤ ዘላቂ ሰላም ህልማችን ነው፤ ናፍቆናል ብለዋል። ሰላም በመኾኑ ጥምቀትን አክብረናል። ሴቶች በየቤታችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን አበክረን እንድንሠራ መወያየት እና መተግበር አለብን” ነው ያሉት።
የዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ታድሎ ብርሃን የተገኘውን ሰላም ዘላቂ እንዲኾን ኀብረተሰቡ እና የጸጥታ ኃይሉ ተናበው መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል። ኀብረተሰቡ በየቀጣናው ተደራጅቶ በውስጡ ያለውን ችግር ማስወገድ አለበት ነው ያሉት።
መንግሥትም ለሰላም ሲል መደራደር ይኖርበታል ነው ያሉት ወይዘሮ ድግሴ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!