
በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከልና የአገር ህልውናን በማስቀጠል ሥራ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ምሁራን መክረዋል።
በጉዳዩ ላይ ከኢዜአ ጋር ውይይት ያደረጉ ምሁራን እንደተናገሩት አሁን በኢትዮጵያ የተከሰተው ዓለምአቀፍ ወረርሽኝ የሰውን ሕይወት ለአደጋ ከማጋለጥ ባለፈ የአገርን ጥቅም የሚያሳጣ ነው። በዚህ ወሳኝ ወቅት ፓርቲዎች ከፖለቲካ ሽኩቻ ወጥተው ወረርሽኙን በጋራ ለመከላከል ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸውም ምሁራኑ አስገንዝበዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና ጠበቃ አቶ ቸርነት ሆርዶፋ እንዳሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕዝብ ውግንና እንዳላቸው የሚያሳዩት በአገር ላይ የተደቀነን አደጋ በጋራ መከላከል ሲችሉ ነው። “በአሁኑ ወቅት ‘ምርጫ ይራዘም፤ አይራዘም’ ከሚልና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ሀሳቦች ዋናውን የአገር ጥቅም እየጎዳ ያለውን ወረርሽኝ እንዳያዘናጉና የፖለቲካ ሽኩቻዎችም ኅብረተሰቡን ወደማይገባ ተግባር እንዳይመሩ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል” ብለዋል።
አቶ ቸርነት እንዳሉት አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች አገርን የከፋ ጉዳት ላይ የሚጥልና ሕዝቡን ለሁከትና ብጥብጥ ሚዳርጉ ሃሳቦች የማንሳት አዝማሚያ ተስተውሎባቸዋል።
“አገርና ሕዝብ የማዳን ሥራ እየተሠራ ባለበት በአሁኑ ወቅት በግልም ይሁን በጋራ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕዝብ መቆማቸውን ማሳየት አለባቸው” ሲሉም ነው ሀሳብ የሰጡት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና የፌዴራሊዝም መምህር ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ በበኩላቸው “ወቅቱ ስልጣን የምንሻማበት ሳይሆን የሰውን ልጅ የማዳን ሥራ ምንሰራበት መሆን አለበት” ብለዋል። በሽታውን መከላከል የሚቻልበትን የተሻለ አማራጭ በማቅረብ ቫይረሱ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ፓርቲዎቹ ጥረት ማደረግ እንደሚጠበቅባቸውም ነው ያመለከቱት።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የህግ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ አብነት ዘውዱ በበኩላቸው ፓርቲዎች እንደ አገር ችግር ሲፈጠር ችግሩን በጋራ በመከላከል የሕዝብ ተቆርቋሪነታቸውን ማሳየት አለባቸው ነው ያሉት። በአገሪቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ እንደ አገር እየተሠራ ያለውን ሥራ ለማገዝም ፓርቲዎቹ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ፓርቲዎች “እስካሁን ለሕዝቡ ተጠቃሚነት ምን ሰርቻለሁ” የሚለውን መገምገም እንደሚገባቸውም ነው ያስረዱት።