የአገው ፈረሰኞች በዓል በድምቀት እንዲከበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተዋል።

44

ባሕር ዳር: ጥር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአገው ፈረሰኞች በዓል በድምቀት እንዲከበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል። የአገው ፈረሰኞች በዓል ጥር 23 በእንጅባራ ከተማ በድምቀት ይከበራል። የአገው ፈረሰኞች በዓል ታሪክ፣ ባሕል እና እሴት የሚገለጽበት ታላቅ እና ደማቅ በዓል ነው። በበዓሉ በርካታ ፈረሰኞች እና እንግዶች ይታደማሉ።

የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ የአገው ፈረሰኞች በዓል በድምቀት የሚከበር በዓል መኾኑን ገልጸዋል። የአገው ፈረሰኞች በዓል እንደ ክልል የቱሪዝም መዳረሻ ከኾኑ ታላላቅ በዓላት መካከል አንደኛው መኾኑንም ተናግረዋል። በክልሉ የተከበሩ የአደባባይ በዓላት አምረው እና ደምቀው መከበራቸውን ያስታወሱት ምክትል ኀላፊው የአገው ፈረሰኞች በዓልም ለበዓሉ ታዳሚዎች እና ጎብኝዎች የተመቸ ኾኖ አምሮ እና ደምቆ እንዲከበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሢሠራ መቆየቱን ነው የተናገሩት።

በዓሉ ታሪክ የሚተላለፍበት በዓል ስለኾነ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ማድረግ የመጀመሪያው ተግባር መኾኑንም ገልጸዋል። በዓሉ ታሪኩን ጠብቆ እና ለጎብኝዎች ምቹ ኾኖ እንዲከበር አስቀድሞ ሢሠራ መቆየቱንም አስታውሰዋል። በበዓሉ ከፈረስ ትዕይንት ባለፈ የአገው ሕዝብ የአመጋገብ ሥርዓት፣ አለባበስ፣ ባሕል፣ ማንነት የሚገለጥበት መኾኑንም አንስተዋል።

በዓሉ የአገው ሕዝብ የእንግዳ ተቀባይነት ይገለጥበታልም ነው ያሉት። የአገው ፈረሰኞች በዓል በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በዓለም ቅርስነት ለመመዝገብ የሚያስፈልጉ መሥፈርቶችን አሟልቶ እንዲሄድ ለማድረግ ቢሮው ሙያዊ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

በበዓሉ ጎብኝዎች በስፋት እንዲገኙ የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ነው ያነሱት። የአገው ፈረሰኞች በዓል ለክልሉ የቱሪዝም ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል። በዓሉ የጥንት ይዘቱን እና ታሪኩን ጠብቆ እንዲከበር ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። በዓሉ ታሪኩ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገር የመጠበቅ፣ የማልማት እና የመንከባከብ ኀላፊነት አለብን ነው ያሉት።

ጎብኝዎች በድምቀት በሚከበረው በዓል እንዲሳተፉ ማድረግ ከባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። በዓሉ ከፍተኛ የቱሪዝም መነቃቃትን ያመጣል ነው ያሉት። የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በድምቀት በሚከበረው የአገው ፈረሰኞች በዓል እንዲታደሙም ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበባሕር ዳር ከተማ የሕዝብ ውይይት እየተደረገ ነው።
Next articleየአፍሪካ ኢነርጂ ጉባዔ በታንዛኒያ እየተካሄደ ነው።