“የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ኢኮኖሚ ስኬት ምሰሶነት ተሸጋግረዋል” ብሩክ ታዬ (ዶ.ር)

62

ባሕር ዳር፡ ጥር 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አጥጋቢ ካልሆነ የአስተዳደር ማዕቀፍ በመውጣት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ እና አማራጭ የፋይናንስ ምንጭነት መሸጋገራቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ.ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት ተቋም ሆኖ የሚያገለግለው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በ100 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል የተቋቋመው በ2014 ዓ.ም ነው። ተቋሙ በስሩ 34 የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በባለቤትነት ያስተዳድራል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ፖስታ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከድርጅቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ.ር) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም አዘጋጅነት በሚቀርበው ”ኢትዮጵያ ኢን ፎከስ” በተሰኘው ፕሮግራም ላይ ተቋሙ ለኢኮኖሚ እድገት ያለውን አበርክቶ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከዚህ ቀደም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የአስተዳደር ቅርጽ በሚፈለገው ሁኔታ ውጤታማ እና ትርፋማ እንዳይሆኑ ከማድረጉ ባለፈ የመንግስትን በባለቤትነት ማስተዳደርን ይገድብ እንደነበር ገልጸዋል። የለውጡ መንግስት ባደረጋቸው ማሻሻያ አማካኝነት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን አመልክተዋል።

ተቋሙ የልማት ድርጅቶቹ ያላቸውን ስትራቴጂካዊ ሀብት በመጠቀም ትርፋማ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል የአስተዳደር መዋቅር የመዘርጋት እና ራሱ ተቋሙን የኢትዮጵያ መንግስት ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት ክንድ የማድረግ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል። በፓሪስ የአክሲዮን ገበያ የዓለም አቀፍ የንግድ ኩባንያዎችን አክሲዮን ላይ መዋዕለ ንዋዩን በማፍሰስ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሠራ ነው ብለዋል።

በዚህም የልማት ድርጅቶቹ አጥጋቢ ካልሆነ የፋይናንስ እና አስተዳደር አቅም ወጥተው በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እየተወጡ እንደሚገኙ ነው የገለጹት። ድርጅቶቹ በኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በባለቤትነት መተዳደራቸው መንግስት ስትራቴጂካዊ ፍላጎቱን እንዲያሳካ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ይፋ የሆነው የኢትዮ ቴሌኮም የ10 በመቶ ድርሻ ሽያጭም ድርጅቶቹ የሀብት ምንጭ መሆናቸውን ማሳያ ነው ብለዋል። የልማት ድርጅቶቹ ልክ እንደ አየር መንገድ ትርፋ የሚያደርጋቸው የንግድ አሰራር እንዲከተሉ በተቀመጠው አቅጣጫ ውጤት እየተገኘ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ማሻሻያ ያደረገበት የአምስት ስትራቴጂም የልማት ድርጅቶች የአገልግሎት እና ምርት ብዝሃነት ማስፋት፣ የኢኮኖሚ አበርክቷቸውን ማሳደግ እና የአቅርቦት ተደራሽነታቸውን ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረጉን ተናግረዋል። ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የማዳበሪያ አቅርቦት፣ ቴሌኮም፣ ዲጂታል ክፍያ እና ሌሎች ከሰው ሕይዎት ጋር የቀጥታ ትስስር ያላቸው ዘርፎችን የያዘው ተቋም በኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ያለውን ድርሻ እያደገ መጥቷል ነው ያሉት።

ተቋሙ ከሚያገኘው ትርፍ ላይ የመንግስትን የንግድ ጉድለት እየሸፈነ እንደሚገኝ እና በቀጣይ አምስት ዓመት ውስጥ አጠቃላይ ጉድለቱን የመሙላት እቅድ መያዙንም ነው ያብራሩት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በቅርቡ በጋምቤላ ክልል በመረቁት ኢትኖ ማይኒንግ የወርቅ ፋብሪካም ድርሻ በመግዛት የፋብሪካውን የስራ አድማስ ለማስፋት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ሙሉ እምነት እንዲኖራቸው የስጋት ቅነሳ ሥራን እንደሚያከናውን አክለዋል። በቢሊዮንች ብር የሚቆጠር ሀብት ያላቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች ኢትዮጵያ ከእዳ ይልቅ ስትራቴጂካዊ ሀብቷ ከፍተኛ እንደሆነ የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግር ውስጥ እየወጣ ያለውን ሚና አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተማሪዎች ምዘገባ እስከ የካቲት 30 2017ዓ.ም ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
Next articleበባሕር ዳር ከተማ የሕዝብ ውይይት እየተደረገ ነው።