የተማሪዎች ምዘገባ እስከ የካቲት 30 2017ዓ.ም ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

74

ደሴ: ጥር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ባለፉት ስድስት ወራት በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ በኮምቦልቻ ከተማ እየገመገመ ነው።

በመንፈቅ ዓመቱ የነበሩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን እየተመከረባቸው ነው። በግምገማው በክልሉ ያሉ ትምህርት ቤቶች በግብዓት፣ በሂደት እና በውጤት ተመዝነው 13 ነጥብ 4 በመቶዎቹ ብቻ ደረጃቸውን ያሟሉ ናቸው ተብሏል። ከግብዓት አንጻር አሁንም በክልሉ የዳስ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ተገልጿል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ፍቅር አበበ በዚህ ዓመት መመዝገብ ከነበረባቸው ተማሪዎች ውስጥ 93 በመቶ የሚኾኑት ተመዝግበው ትምህርታቸውን አየተከታተሉ ነው ብለዋል። የመጽሐፍት አቅርቦት ከባለፈው ዓመት በተሻለ ሁኔታ ስርጭት መደረጉን ጠቅሰዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሰጠ ታደሰ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ከ170 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን ተናግረዋል። ችግሩን ለመቅረፍም ከማኅበረሰቡ ጋር ውይይት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

ትምህርት ተቋማት ደረጃቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ አስተማማኝ ሰላም ወሳኝ መኾኑን የገለጹት ኀላፊው የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል እና የትምህርት ቤቶች ገጸታ ላይ ለውጥ ለማምጣት የማኅበረሰቡ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ኢየሩስ መንግሥቱ የጸጥታ ችግሩ የክልሉን ትምህርት እየጎዳው መኾኑን ተናግረዋል። በዚህ ዓመት ይመዘገባሉ ተብሎ ታቅዶ ከነበረው 7 ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ ከ4 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑት ተማሪዎች አልተመዘገቡም ብለዋል። በትምህርት ላይ ያሉት 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ከተመዘገቡት ተማሪዎች ውስጥም ከ400 ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ ተቋማቱ አልመጡም ነው ያሉት።

የተማሪዎች ምዝገባው በልዩ ሁኔታ እስከ የካቲት 30 ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ምክትል ኀላፊዋ እስከ ሐምሌ ወር መጨረሻ ትምህርት እንደሚሰጥም ገልጸዋል። ዘግይተው የጀመሩ ተማሪዎችን የማብቃቱም ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በክልሉ 251 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጡ መኾናቸውን እና 29 ትምህርት ቤቶች ደግሞ የአዳር ጥናት ፕሮግራም ጀምረዋል ብለዋል።

የግምገማ መድረኩ ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ዘጋቢ፦አንተነህ ጸጋዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article340 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next article“የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ኢኮኖሚ ስኬት ምሰሶነት ተሸጋግረዋል” ብሩክ ታዬ (ዶ.ር)