
አዲስ አበባ: ጥር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት አምስት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ በተለይም በእርሻ እና በአበባ ልማት ዘርፍ የተሠሩ ተግባራትን አስመልክቶ ግብርና ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥቷል። የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ.ር) በሰጡት መግለጫ ዘርፉ አራት ቁልፍ ዓላማዎችን የያዘ፣ ፖሊሲዎችን እና የሕግ ማዕቀፎችንም ያካተተ የ10 ዓመት ዕቅድ ይዘን እየሠራን ነው ብለዋል።
አራቱ ቁልፍ ዓላማዎችም በምግብ እና የሥርዓተ ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ በሀገር ብሎም በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ፤ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን በዓይነት፣ በጥራት እና በብዛት ማምረት፣ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ የሚኾኑ ጥሬ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ ማምረት እና በገጠራማው አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶችን እና ሴቶችን በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ ማድረግ እንደኾኑ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
እየተጠናቀቀ ባለው የመኸር ወቅት ወደ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው። ምርት ያልተሰበሰበባቸውን ቦታዎች ሳይጨምር እስካሁን ባለው 101 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ተሰብስቦ ገብቷል፤ በቀሪ ጊዜያትም ያልተሰበሰበውን አጠናቅቀን እቅዳችንን እናሳካለን ነው ያሉት።
በመስኖ ስንዴ በ2017 ዓ.ም 4 ነጥብ 27 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን እና 173 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ እንደኾነም ሚኒስትር ዴኤታው በመግለጫቸው አመላክተዋል። እስካሁን ባለው መረጃ መሠረትም 3 ነጥብ 41 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ መኾኑን አንስተዋል።
በአጠቃላይ በስንዴ ብቻ በበልግ፣ በመኸር እና በመስኖ እንደ ሀገር 340 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ እንደኾነም ሚኒስትር ዴኤታው መለስ መኮንን (ዶ.ር) ጠቅሰዋል።
እንደ ሀገር 97 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት በዓመት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው በአትክልት እና ፍራፍሬ ዘርፍም ትልቅ ለውጥ የመጣበት ሥራ መከናወኑንም በመግለጫቸው አንስተዋል።
ዘጋቢ: ቤቴል መኮንን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!