
ባሕር ዳር: ጥር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በኬኒያ ናይሮቢ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ተቋማዊ ማሻሻያ ሥብሠባ ላይ ተካፍለዋል።
ፕሬዚዳንቱ በሥብሰባው ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረት ተቋማዊ ማሻሻያ አጀንዳ ስኬታማ ትግበራ ቁርጠኛ መኾኗን ገልጸዋል። በአህጉሪቱ ለተገኙ እመርታዎች ዕውቅና በመስጠት የአፍሪካ ኅብረትን አቅም ሙሉ በሙሉ ዕውን ለማድረግ የሚቀሩ ጉዳዮች ላይ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
አካታችነትን ማረጋገጥ የገንዘብ ሉዓላዊነትን ማስከበር፣ የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳዎችን ማስቀደም እና ማስተካከል፣ ጠንካራ የንግግር ባሕልን ማዳበር፣ በዓለም አቀፍ መድረክም የኅብረቱን ትስስርን ማሳደግ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ነጥቦች መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
ለተፈፃሚነቱም ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መኾኗንም አረጋግጠዋል። ኢቢሲ እንደዘገበው በአፍሪካ ኅብረት ተቋማዊ ማሻሻያ የሥብሠባ መድረክ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት እና የሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል።
በሥብሠባው የሚነሱ ሀሳቦችን በማካተት በቀጣይ በየካቲት ወር በአዲስ አበባ በሚካሄደው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ምክረ ሀሳብ እንደሚነሳ ይጠበቃል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!