
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 25/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአሜሪካ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ጾታን መሠረት ያደረገ የክፍያ ልዩነቱ እስከሚስተካከል ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
በአሜሪካ ሴት የእግር ኳስ ተጫዋቾች ከወንድ አቻወቻቸው እኩል ደመወዝ እንዲከፈላቸው በፍርድ ቤት ጭምር ጠይቀው ነበር፤ ፍርድ ቤቱ ግን ‘‘ጥያቄው ቅቡል አይደለም፤ ያነሰ ተከፋይም አይደላችሁም’’ ብሎ ውድቅ አድርጎታል፡፡ ጥያቄውን ወደ ሕግ የወሰዱት 28 የአሜሪካ ሴት ብሔራዊ ቡድን አባላት ናቸው፡፡
እስከ 66 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተጨማሪ ክፍያ ነበር የአገሪቱን እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በሕግ የጠየቁት፡፡ ፍርድ ቤቱ ጥያቄያቸውን ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ ተጫዋቾቹ ይገባኝ እንደሚጠይቁም የቡድኑ ቃል አቀባይ ሞሊ ሌቪሰን ተናግራለች፡፡ ‘‘በውሳኔው ደንግጠናል፤ ቢሆንም ግን ተስፋ ሳንቆርጥ ትግላችንን እንቀጥላለን’’ ብላለች፡፡ ‘‘በጥያቄያችን ፍትሐዊነት ጥርጥር የለንም፤ ሴት ስለሆንን ብቻ ከወንዶች ያነሰ ደመወዝ መከፈሉ ትክክል አይደለም’’ ስትልም ቃል አቀባይዋ መናገሯን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአሜሪካ ፕሬዝዳታዊ ምርጫ የዴሞክራቱ ዕጩ ጆይ ባይደን ‘‘ትግላችሁ ትክክለኛ ነው፤ ተግታችሁ ቀጥሉ’’ ሲሉ ከሴት እግር ኳስ ተጫዋቾቹ ጎን መሰለፋቸው ተሰምቷል፡፡ ‘‘በአሜሪካ እግር ኳስ እኩል ክፍያ መኖር አለበት፡፡ ካልሆነ ግን እኔ ፕሬዝዳንት ስሆን ለዓለም ዋንጫ ማስተካከያው ይደርሳል’’ የሚል ሐሳብም ባይደን ሰንዝረዋል፡፡
ሴት ተጫዋቾቹ በደመወዝ ብቻ ሳይሆን ለልዩ ልዩ ውድድሮች ወደተለያዩ ሀገራት ሲሄዱ በቂ ክፍያና ጥቅማጥቅም እንደማይሰጣቸውም አንስተዋል፡፡ የአሜሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደግሞ ነገሩን በድርድር መፍታት እንደሚሻልና በፍርድ ቤት መጠየቁ አስፈላጊ አለመሆኑን እየገለጸ ነው፡፡
በአብርሃም በዕውቀት