ምክር ቤቱ ሁለት የብድር ስምምነቶችን አጸደቀ።

47

ባሕር ዳር: ጥር 19/2017 ዓ.ም( አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ ልዩ ስብሰባውን አካሂዷል።

ምክር ቤቱ ባካሄደው አንደኛ ልዩ ስብሰባ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር ጋር ያደረጋቸውን ሁለት የብድር ስምምነቶችን አጽድቋል። የብድር ስምምነቶቹ የፋይናንስ ዘርፉን ለማጠናከርና የመንግሥት አገልግሎትን ለማሻሻል የሚውሉ ናቸው ተብሏል። የብድር ስምምነቶቹን አስመልክቶ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ.ር) ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር ጋር ያደረገችው የ700 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት እና ተወዳዳሪነት የበለጠ ለማሻሻል ያስችላል ብለዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፒታል አቅምን እንደሚያሳድግ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ብድሩ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን አሠራር ለማዘመን ያስችላልም ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት የዕዳ ጫናዋ እየቀነሰ መምጣቱንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር ለዘመናዊ የመንግሥት አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ70 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነትም ለምክር ቤቱ ቀርቧል።

ምክር ቤቱ በብድር ስምምነቶቹ ላይ ከተወያየ በኃላ ስምምነቶቹን በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን ኢዜአ ዘግቧል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሠረት የጣሉ ተግባራት ተከናውነዋል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየአፍሪካ ኅብረት አጀንዳዎችን ማስቀደም እና ጠንካራ የንግግር ባሕልን ማዳበር እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።