“ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሠረት የጣሉ ተግባራት ተከናውነዋል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

30

ባሕር ዳር: ጥር 19/2017 ዓ.ም( አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሠረት የጣሉ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ እና ውጥኖችን የተመለከተ ኤግዚቢሽንና አውደ ጥናት አካሂደናል ብለዋል።

መንግሥት ከለውጡ ማግሥት 2012 ዓ.ም ጀምሮ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ሀገራችን የቴክኖሎጂ ዕድገት ዕድሎችን እንድትጠቀም የሚያስችሉ ተግባራትን አከናውኗል ነው ያሉት።

የዲጂታል መሠረተ ልማት በመሥፋፋቱ የፋይናንስ እና የክፍያ ሥርዓት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥት አገልግሎቶችን የማዘመን፣ ወደ ዲጂታል የማሸጋገር እና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲጨመር መደረጉን ነው ያመላከቱት።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራዎች የተቀናጁ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ የሃብት ብክነትን የማያስከትሉ፣ የዜጎቻችንን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና ፈጣን ለውጥ የሚያመጡ እንዲሆኑ መንግሥት የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የመጀመሪያውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራ እያጠናቀቅን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ 5 ዓመታት ሥራ ላይ የሚውል የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ዝግጅት እያጠናቀቅን እንገኛለን ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአሕጉር አቀፍ የእንስሳት ጤና ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው።
Next articleምክር ቤቱ ሁለት የብድር ስምምነቶችን አጸደቀ።