
አዲስ አበባ: ጥር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 26ኛው የእንስሳት ጤና ጉባኤ ከጥር 27 እስከ 30/2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚከበር የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ጉባዔው በአሕጉር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የተናገሩት እና የቀኑን አከባበር አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ.ር) ናቸው።
ቀኑ “የእንስሳት ጤና ለምግብ እና ሥነ ምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና ለኅብረተሰብ ጤና” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከበር ነው የገለጹት። መንግሥት ለእንስሳት ሃብት በሰጠው ትኩረት እና ኢትዮጵያ ካላት ትልቅ የእንስሳት ሃብት አኳያ በአሕጉር ዓቀፍ ደረጃ ጉባኤውን እንድታዘጋጅ ተመርጣለች ብለዋል።
ከ54ቱም የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች በጉባዔው ለመሳተፍ አዲስ አበባ እንደሚገኙም ተናግረዋል በመግለጫው።
በጉባኤው የእንስሳት ጤና አስተዋጽኦ በምግብ እና በሥነ ምግብ ምን ይመስላል? በሚለው እና ከበሽታ ነጻ ቀጣና በአፍሪካ ማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ የእንስሳት በሽታ መከላከል ዙሪያ ውይይቶች እንደሚደረጉም አንስተዋል።
የእንስሳት ጤና ለኅብረተሰቡ ጤና ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የጠቀሱት ሚኒስትር ድኤታው በእንስሳት አያያዝ እና ደኅንነት ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፎች የሚቀርቡበት፣ ልምድ የሚቀሰምበት፣ ውይይቶች የሚካሄዱበት፣ ኢትዮጵያም በእንስሳት ጤና ዙሪያ ያላትን ተሞክሮዎች የምታካፍልበት ጉባዔ እንደሚኾን ሚኒስትር ድኤታው ተናግረዋል።
300 የሚኾኑ ተሳታፊዎች በጉባዔው ላይ እንደሚገኙም ተገልጿዋል ።
ዘጋቢ፦ ቤቴል መኮንን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!