
አዲስ አበባ: ጥር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመግባቢያ ሥምምነቱን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት እና በከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የፌዴራል የመንግሥት ሕንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኢንጅነር ዳዊት ማሀሪው ፈርመውታል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ተቋሙ ከአሁን በፊት አገልግሎት የሚሰጥበት ሕንጻ በቂ እና ደረጃውን የጠበቀ ባለመኾኑ ምቹ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት አስቸጋሪ እንደ ነበር አስታውሰዋል። የሕንጻ ፕሮጀክቱ 5 ሺህ 900 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ሲኾን ግንባታውን በ600 ቀናት ለማጠናቀቅ መታቀዱን አንስተዋል።
የግንባታ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለሠራተኛው ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ ለተገልጋዩ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል። የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ግንባታውን ለማጠናቀቅ 600 ቀናትን እንደሚፈጅ በዕቅድ ቢያዝም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከታቀደለት የጊዜ ገደብ ቀድሞ በጥራት እና በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የግንባታ ፕሮጀክቱ ተቋራጭ ይርጋለም ኮንስትራክሽን ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሲኾን ማኅበሩ ግንባታውን በታለመለት የጊዜ ገደብ እና በጥራት ሠርቶ ለማስረከብ ቁርጠኛ መኾናቸውን የማኅበሩ ባለቤት ኢንጅነር ዘላለም ወልደአማኑኤል ተናግረዋል።
የግንባታ ፕሮጀክቱ ባለ 16 ወለል ሕንጻን የሚያካትት ሲኾን 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገደማ በኾነ ወጭ እንደሚገነባም ተጠቁሟል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!