በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ የጋራ አቅጣጫን መተለም መሠረታዊ ተግባር ነው።

41

ባሕር ዳር: ጥር 19/2017 ዓ.ም( አሚኮ) ሀገራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ በሚገኙ ባለድርሻ አካላት መካከል ለተፈጠሩ አለመግባባቶች በመነጋገር መፍትሔ እንዲመጣ የሚያደርግ ዲሞክራሲያዊ ሂደት ነው።

ሂደቱ ተከናውኖ አመርቂ ውጤት ባስመዘገበባቸው ሀገራት ባለድርሻ አካላት በሀገራዊ ምክክር የጋራ አቅጣጫን በማበጀት አንኳር በኾኑ ሀገራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ መግባባትን ፈጥረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ውስጥ በተወካዮቻችን አማካኝነት ስንሳተፍ የጋራ መንገዶችን መሥርተን መግባባት ላይ ለመድረስ የትኞቹ ተግባራት ከተሳታፊ ባለድርሻ አካላት ይጠበቃሉ ? የሚሉትን አስፍሯል።

👉የጋራ እሴቶችን መፈለግ

በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ላይ ዜጎች አንድ የሚያደርጓቸው እሴቶቻቸው ላይ ማተኮራቸው በሂደቱ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚያደርጉትን ጉዞ ፍሬያማ ያደርገዋል፡፡

የሰው ልጆች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስፈልጋቸውን ክብር፣ ፍትሕ እና እንዱ ለሌላው መኖር ለሀገር አንድነት አስፈላጊ መኾናቸውን በመረዳት፤ እነዚህንም እንደመርህ መከተል የጋራ አቅጣጫን ለመተለም በእጅጉ ያግዛል፡፡

👉ከተለያዩ አቋሞች ጀርባ ያሉ ፍላጎቶችን መረዳት

የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ወደ ምክክር መድረኮች ሲመጡ የተለያዩ አቋሞችን ሊያንፀባርቁ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡

አንዳንድ ጊዜም ጥቂት የማይባሉ ባለድርሻ አካላት በእጅጉ የሚራራቅ አቋም መያዛቸው መግባባት ላይ ለመድረስ የሚደረገውን መንገድ ረዥም ያደርጉታል፡፡ ሆኖም ግን አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ እነዚህ አቋሞች መነሻቸው ያልተመለሱ እና ቁርሾን የፈጠሩ የረዥም ጊዜ ፍላጎቶች መኾናቸው ነው፡፡

በመሆኑም ይህን ማድረግ አንዳችን የሌላችንን ሕመሞች እና ፍላጎቶችን በመረዳት የጋራ አቅጣጫን ለመተለም በእጅጉ ይረዳል፡፡

👉ለትንንሽ ስኬቶች ዕውቅና መስጠት

የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ረጅም እና የብዙ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚፈልጉ ከመኾናቸው አንጻር እጅግ በርካታ ጉዳዮች በሂደቱ ተነስተው ስምምነት ላይ ለመድረስ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡

ሆኖም ግን ሂደቱ የሚፈጥራቸውን ትንንሽ ስኬቶች አጉልቶ በማየት እና ከተገኙ ስኬቶች በመነሳት ትልልቅ እና ውስብስብ ችግሮችን መፍታት ሂደቱን ውጤታማ ያደርገዋል፡፡ ይህም የጋራ አቅጣጫ ለመተለም የሚደረገውን ጥረት ያጠናክረዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባለፉት ወራት ከ597 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት ተስቧል።
Next article“ትልቅ ሀገር እና ሕዝብ የሚመራ ፓርቲ በመኾኑ እና ተጠባቂ ውሳኔዎችን የሚያሳልፍ በመኾኑ የብልጽግና ጉባኤው ተጠባቂ ነው ” አደም ፋራህ