
ባሕር ዳር: ጥር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ “የሠባሩ አጽሙ ቅዱስ ጊዮርጊስ” ዓመታዊ ክብረ በዓል በድምቀት ተከብሯል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ከሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ ባለፈ ለባሕር ዳር ከተማ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
በበዓሉ ላይ ትምህርት እና አባታዊ ቡራኬ የሰጡት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ አብርሃም እግዚአብሔር ባሕር ዳርን በጣና እና በግዮን ባርኳታል ብለዋል።
ቤተክርስቲያን ሁልጊዜም ታሪክ ጠባቂ እንደኾነች ገልጸዋል። በዓሉ እንደቀደመው ሁሉ በጣና ሐይቅ እንዲከበር እና ታሪክ እንዲጠበቅ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። በዓሉ በድምቀት መከበሩንም ገልጸዋል።
ሃይማኖትን በሃይማኖታዊ ሥርዓቱ፣ ባሕልንም በባሕል ወጉ ማክበር ይገባል ነው ያሉት። ስንደማመጥ፣ ስንተባበር፣ ስንስማማ እጅግ ያምርብናል ያሉት ብጹዕነታቸው ጉዳታችን አለመተባበራችን፣ አለመናበባችን፣ አለመስማማታችን፣ በዘፈቀደ መመላለሳችን ነው ብለዋል።
ሀገርን ከፍ ለማድረግ፣ እንደ ሃይማኖት በሃይማኖት ጸንቶ ለመኖር ፍቅርን እና ሰላምን ገንዘብ አድርጎ መሄድ መልካም ነው ብለዋል ብጹዕነታቸው።
ኢትዮጵያዊ ባሕሪ ለሀገር እና ለድንበር ዘብ መቆም እንጂ እርስ በእርስ መገዳደል አለመኾኑንም ገልጸዋል። ሰላም እንዲመጣ ጸልዩ፣ ሰላምንም አውጁ ነው ያሉት።
ገፊም፣ ተገፊም፣ አሳዳጅም ተሳዳጅም ሳይኖር፣ ሁሉም ነገር በሰላም እንዲፈታ መጸለይ እና ሰላምን ማወጅ ይገባል ነው ያሉት።
በርካታ ኢትዮጵያውያን እየተሰደዱ በሰው ሀገር ዋጋ እየከፈሉ መኾናቸውን ያነሱት ብጹዕነታቸው ኢትዮጵያውያን ወገኖች በሀሰተኛ መረጃዎች እየተታለሉ እንዳይሰደዱም አሳስበዋል።
ወጣቶች እየተሰደዱ እና በዚያው እየቀሩ እናቶቻቸውን እንዳያሳዝኑም አባታዊ መልዕክታቸውን አቅርበዋል።
አብረን እንኑር፣ አብረን እንሥራ ያኔ ኢትዮጵያዊነት ከፍ ይላል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!