
ባሕርዳር: ጥር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ከክልሉ የተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል። በምክክሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው ( ዶ.ር) የሚዲያ እና የኮሙዩኒኬሽን መዋቅሩ የክልሉ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እንዲመጣ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል። ሚዘናዊ፣ እውነተኛ እና ጥራት ያላቸው መረጃዎችን በማድረስ በሀሰተኛ መረጃዎች ተደናግሮ የነበረውን የመመለስ፣ እኩይ እና አፍራሽ አጀንዳዎችን የማምከን ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
የሚዲያ እና የኮሙዩኒኬሽን መዋቅሩ በሠራው የተቀናጀ ሥራ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለሕዝብ ሲያቀርቡ የነበሩ አካላት ሰሚ እንዲያጡ ማድረጉንም ተናግረዋል። የኮሙዩኒኬሽን መዋቅሩ ተከታታይ እና ፈጣን መረጃዎችን ለሕዝብ በማድረስ በኩል ትልቅ ሥራ መሥራቱን እና አሁንም በትኩረት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በክልሉ ያለውን ትክክለኛ እውነታ ለሕዝብ በማድረስ እና መፍትሔ በማመላከት ትልቅ ሥራ መሥራቱንም ገልጸዋል። በተሠራው ሥራ የክልሉን እውነታ መግለጥ እና ማሳወቅ መቻሉንም ተናግረዋል።
አሁን ላይ የክልሉ ሰላም ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ ለልማት እና ለመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ከሰላም ሥራዎች ጎን ለጎን የልማት ሥራዎቻችንም አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት። የሚዲያ እና የኮሙዩኒኬሽን መዋቅሩ እየሠራው ያለው ሥራ የሚደነቅ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው መረጃዎችን በፍጥነት እና በብዛት ከማድረስ ባሻገር የመረጃ ጥራት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ተዓማኒ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለሕዝብ ማድረስ እንደሚገባም አሳስበዋል። የክልሉ ሰላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን መዋቅር፣ በቅንጅት እና በአንድነት መሥራት አለበት ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!