“በዓሉ የከተማችንን የቱሪዝም መዳረሻነት፣ ሰላም እና ልማት የምናሳይበት ነው” ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ

24

ባሕር ዳር: ጥር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ “የሰባር አፅሙ ቅዱስ ጊዮርጊስ” ዓመታዊ ክብረ በዓል በድምቀት እየተከበረ ነው። የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ከሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ ባለፈ ለባሕር ዳር ከተማ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
በበዓሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳር እና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ ሊቃውንት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና ምዕምናን ተገኝተዋል።

በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ በባሕር ዳር ከተማ እንብርት ላይ የሚገኘው፣ ለባሕር ዳር ከተማ የከተማነት ስያሜም መነሻ የኾነው የባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል የነገሥታቱ አሻራ ያረፈበት መኾኑን ተናግረዋል። በነገሥታቱ ዘመን በሥርዓቱ እና በትውፊቱ መሠረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ከመንበረ ክብሩ እየወጣ ሐይቁን እየባረከ ይመለስ እንደነበር አስታውሰዋል።

እንደ ቀደመው ሁሉ ዛሬም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ እና ትውፊቱ በጠበቀ መልኩ የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓል በድምቀት እንደሚከበር ነው ያነሱት። በተለይም ጥርን ከባሕር ዳር ጋር በመያያዝ በታላቅ ሥርዓት እየተከበረ መኾኑን ነው የገለጹት። በዓሉ የከተማችንን የቱሪዝም መዳረሻነት፣ ሰላም እና ልማት የምናሳይበት፣ ከተማችንን ከፍ የምናደርግበት ነው ብለዋል። ከተማ አሥተዳደሩ ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር በመኾን በዓሉን በድምቀት ለማክበር ሁልጊዜም ዝግጁ መኾኑንም ተናግረዋል። በዓሉ የሰላም፣ የደስታ እና የፍቅር እንዲኾንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሃይማኖታዊ በዓላትን ከቱሪዝም ጋር ማስተሳሰር ቱሪዝሙን ለማነቃቃት ያግዛል።
Next articleተዓማኒ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለሕዝብ ማድረስ እንደሚገባ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) አሳሰቡ።