
ባሕር ዳር: ጥር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር የሚከበሩ በዓላት ከመንፈሳዊ ጠቀሜታቸው በተጨማሪ ቱሪዝምን ስለሚያነቃቁ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲሉ የባሕር ዳር ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ነዋሪ እና በፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል አገልጋይ ሄኖክ እንዳላማው የሰባር አፅሙ ጊዮርጊስ በዓል መንፈሳዊ ይዘቱን ሳይለቅ ሀገር አቀፍ ኾኖ በሀገር ደረጃ እንዲከበር እንፈልጋለን፤ ጣናን ይዘን የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችም እንዲመጡ ማድረግ አለብን፤ ጣናን እንድንከባከብም ያደርገናል ብሏል።
ሌላኛዋ የበዓሉ ተካፋይ እና ዘማሪ አበባ ታደሰ የሰባር አፅሙ ጊዮርጊስ በዓል በቤተ ክርስቲያን ከዋዜማው ጀምሮ ከአባቶች ጋር ስናገለግል እና ስናከብር አድረናል ብለዋል።
በዓሉ በባሕር ዳር ከጣና ጋር ተያይዞ መከበሩ ከሃይማኖታዊ በረከት በተጨማሪ ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ ጎብኝዎችን ይስባል፤ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ባሕሎቻችንም ለማስተዋወቅ የሚጠቅም እንደኾነም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላት፤ ይህም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያለው ደግሞ የበዓሉ ተካፋይ እና ዘማሪ መልሰው ዘላለም ነው።
ሃይማኖታዊ በዓላትን ከቱሪዝም ዘርፍ ጋር ማስተሳሰሩ ቱሪዝሙን ያነቃቃልናል፤ እናም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!