“ማኅበራዊ ሚድያው ሲፈተሽ”

25

ባሕር ዳር: ጥር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ እኔ በውጭ እግር ኳስ ፍቅር የተለከፋችሁ ከኾናችሁ የጥር የዝውውር ወቅት ከተከፈተበት ጊዜ አንስቶ በምትሰሟቸው ዜናዎች መደነቃችሁ አይቀርም፡፡
የዜናዎቹ አስደናቂነት ብዙ ክለቦች በጥሩ የዝውውር ወቅት በርከት ያሉ ተጨዋቾችን ማስፈረማቸው አይደለም፡፡ የመረጃዎቹ አስገራሚነት ክፍተቶች ያሉባቸው ክለቦች ሳይቀሩ ክፍተቶቻቸውን ለመድፈን የጥሩን የዝውውር ወቅት እንደ መልካም አጋጣሚ አለመጠቀማቸውም አይደለም፡፡
ከአውሮፓ ሊጎች የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግን ያኽል የተመልካች ቁጥር ያለው ሊግ ያለ አይመስለኝም፤ አይመስለኝም ያልኩት ጥናት ላይ የተመሠረተ መረጃ ስለሌለኝ ነው፤ ያም ቢኾን ግን በሀገራችን ውስጥ ሳይቀር የማንቸስተር ዩናይትድ፣ የአርሰናል፣ የሊቨርፑል፣ የቼልሲ እና የሌሎችም ክለቦች ደጋፊዎች በርካታ እንደኾኑ በድፍረት መናገር እችላለሁ፡፡

አሁንም የትዝብቴ ማጠንጠኛ ለምን እኛ ኢትዮጵያውያን የራሳችን የእግር ኳስ ክለቦች እያሉን አሻግረን የውጪዎቹን እንደግፋለን? የሚልም አይደለም፤ ይልቁንም በጥር የዝውውር መስኮት አብዛኛው የማኅበራዊ ገጾች መረጃዎች ለምን የተጨዋቾች ዝውውር ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ኾኑ? ለምንስ የዝውውር መረጃዎቹ አብዛኞቻችን በምንደግፋቸው ክለቦች ዙሪያ ብቻ የሚያጠነጥኑ ኾኑ? መረጃዎቹን እንድናምናቸው የሚደረጉት የውሸት ቅቦችስ ምን የሚያስተምሩን ነገር አለ? በሚሉት ሃሳቦች ዙሪያ ጥቂት ማውጋት ፈልጌያለሁ፡፡
ከላይ ለመጠቆም የፈለኩትን የዝውውር መረጃ በእንግሊዙ የሰሜን ለንደን ክለብ በአርሰናል ምሳሌነት ለማሳየት ልሞክር፡፡
አርሰናል በጥር የዝውውር መስኮት አንድ ኹነኛ አጥቂ ማስፈረም ይኖርበታል የሚለውን ሃሳብ የገዙ የማኅበራዊ ገጾች ከታቢዎቻችን ወይም ተንታኞቻችን አርሰናልን ከተለያዩ ክለቦች አጥቂ ተጫዋች ለማስፈረም ከጫፍ መድረሱን ነግረውናል፡፡ እኔ ይሄን ትዝብት እስከጻፍኩበት ጊዜ ድረስ ግን አንድም አጥቂ ወደ አርሰናል ክለብ አላመራም፡፡

የኔ ትዝብት ለምን አርሰናሎች በዚህ ልክ ተወርቶላቸው አጥቂ አላስፈረሙም? የሚልም አይደለም፡፡ ነገሩ ያለው ወዲህ ነው፡፡ በማኅበራዊ የትሥሥር ገጾች የሚለቀቁልን መረጃዎች እኛ ማየት፣ መስማት እና ማንበብ የምንፈልጋቸው እንጂ እውነት የኾኑ መረጃዎች እንዳልኾኑ ከዚህ ምሳሌ መረዳት እንችላለን፡፡
እነዚህ በሰው ፍላጎት ላይ መሠረት ተደርገው የሚሰራጩ የሃሰት መረጃዎች የሌሎች የማኅበራዊ ገጾች መረጃዎች ነጸብራቅ ኾነው ሊወሰዱ ይችላሉ የሚል የግል አተያይ አለኝ፡፡
እነዚህን የጭምጭምታ ወይም የሃሰት መረጃዎች እውነት ለማስመሰል የሚኬደው ርቀትም የሌሎች መረጃዎች ተምሳሌት አይኾኑም ለማለትም እቸገራለሁ፡፡ ፋብሪዚዮ ሮማኖ የተባለው የስፖርት ጋዜጠኛ ታማኝ የዝውውር መረጃዎችን ለዓለም ሕዝቦች እንደሚያደርስ የተገነዘቡ የፌስ ቡክ ምንደኞች የሱን ስም በዋቢነት እያስገቡ ብዙ የሐሰት መረጃዎችን ሲያሰራጩም ማየት የተለመደ ኾኗል፡፡

“ዛሬ ትኩስ እና ያልተሰሙ የዝውውር ዜናዎችን ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ፤ በቅድሚያ ግን ገጼን ላይክ፣ ሼር፣ ሰብስክራይብ… አድርጉ“ ብሎ የሚጀምረው የማኅበራዊ ሚዲያዎች ሸቃይ እከሌ የሚባለው ተጨዋች ዝውውሩን አጠናቅቆ ለሕክምና ምርመራ ወደ እከሌ ክለብ ተጉዟል፣ ወይም ደግሞ መረጃውን ያገኘሁት ከፋብሪዚዮ ሮማኖ እና ከክለቡ ድረ ገጽ ነው ሲላችሁ ከማመን ውጭ ምርጫ እንዳይኖራችሁ አድርገው ነው፡፡

ለዚህ ዓይነቱ የሐሰት መረጃ የተባላችሁትን ድጋፍ አድርጋችሁ እናንተም የሐሰቱ አጋሪ መኾናችሁ ግን የማኅበራዊ ትሥሥር ገጾችን የአጠቃቀም ውስንነት እንዳለብን ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል፡፡
በአብነት ያነሳሁትን የጥር ወር የተጨዋቾች ዝውውር የተሳሳቱ መረጃዎች እዚሁ ላይ ገታ አድርጌ ሌሎች በማኅበራዊ ገጾች የሚሰራጩ የተሳሳቱ ወይም የተዛቡ መረጃዎችን ጉዳይ በትይዩ ለማየት ልሞክር፡፡
አንድን ሃይማኖት፣ ብሔርን፣ ቋንቋን፣ ግለሰብን፣ መንግሥትን፣ ቡድንን ወይም ሌላን በተሳሳተ መረጃ ለመወንጀል አሳማኝ የሚመስሉ የመረጃ ምንጮችን (ከላይ እንደገለጽኩት ፋብሪዚዮ ሮማኖ ያሉ ሰዎችን ወይም ተቋማትን) በመጠቀም ምን ያህል የተሳሳቱ መረጃዎችን እንድናገኝ እና እርስ በርሳችን እንድንጋጭ ተደርገናል? መልሱን ለህሊናችሁ ልተወው፡፡

የሚሰጡን መረጃዎች እኛ የምንፈልጋቸው ወይም ለኛ ሥነ ልቦና የቀረቡ እንዲኾኑስ ምን ያኽል ጥረት እንደሚደረግስ አስተውላችኋል? ለማንኛውም በፌስ ቡክ፣ በቲክቶክ፣ በቴሌግራም ወይም በሌሎች መረቦች ለሚገኝ ጥቂት ምንዳ ሲባል ብዙዎችን የሚጎዳና ሀገርን ሰላም የሚያሳጣ ነገር ለምንሠራ ሰዎች ጊዜው ወደ ቀልባችን የምንመለስበት ይሁንልን እላለሁ፡፡

ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሚናፈቀው ዋንጫ !
Next articleሃይማኖታዊ በዓላትን ከቱሪዝም ጋር ማስተሳሰር ቱሪዝሙን ለማነቃቃት ያግዛል።