
ባሕር ዳር: ጥር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን በመመስረት ትልቅ ባለውለታ ናት።
ከመመስረት በተጨማሪም በመጀመሪያዎቹ ውድድሮች በመሳተፍ እና ውድድሩን በማዘጋጀትም ጭምር የእግር ኳስ ሀገር ናት። ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ማሸነፏ ደግሞ በመሰረተችው ውድድር የምትናገረው ታሪክ እንዲኖራት አድርጓል።
ጊዜው 1954 ዓ.ም ነው። ሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአዲስ አበባ ተደግሷል። አንደኛው እና ሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሱዳን እና ግብጽ ተከናውኖ ግብጽ አሸናፊ ኾናለች።
ሦስተኛው የአፋሪካ ዋንጫ በአዲስ አበባ በያኔው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታድየም ሲካሄድ ኢትዮጵያ አዘጋጅ ነበረች፡፡
በዚህ ጨዋታም ቱኒዚያ፣ ኡጋንዳ፣ ኢትዮጵያ እና ግብጽ የተሳተፉበት ነበር። አራቱ ቡድኖች በዕጣ ኢትዮጵያ ከቱኒዚያ እና ግብጽ ከኡጋንዳ ተመድበውም ተጫወቱ።
ጥር 6/1954 ዓ.ም ለዋንጫ ለመድረስ ኢትዮጵያ ከቱኒዚያ ተጫወቱ። የደጋፊው ስሜት የተለየ ነበር። ምክንያቱም ባለፉት ዋንጫዎች ብሔራዊ ቡድኑ ከመሳተፍ ውጭ ድል አላስመዘገበም ነበርና ነው።
በጨዋታው ኢትዮጵያ 4ለ2 አሸነፈች። በዚያ በኩል ደግሞ ግብጽ እና ኡጋንዳ ተጫወቱና ግብጽ አሸነፈች። ለዋንጫ ኢትዮጵያ ከግብጽ ተፋጠጡ።
ሁለቱ ቡድኖችም ያደረጉት ጨዋታ በኢትዮጵያ 4ለ2 አሸናፊነት ተጠናቀቀ። አምበሉ ሉቺያኖ ዋንጫውን ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ ተቀበለ። በአፍሪካ ዋንጫም ብቸኛው ድልም ይህ ኾነ። ይህ ድል ከተገኘ በዚህ ሳምንት 63 ዓመት ሞላው።
በውድ ልጆቹ ከፍ ያለው ሰንደቅ!
ጥር 12 ቀን 1933 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ከዛሬ 84 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ መሬት ገብተው ኦሜድላ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የሰቀሉበት ዕለት ነበር፡፡
ኢትዮጵያ በጣሊያን ወራሪ ኀይል በተወረረች ጊዜ ንጉሡ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያን ጉዳይ በጄኔቫ ለሊግ ኦፍ ኔሽን እንዲያቀርቡ ስምምነት ላይ ተደርሶ ወደዛው አቀኑ፡፡ ይሁን እንጂ ውሳኔው በአንድ ድምፅ ባለመኾኑ በርካታ ተሳታፊዎች፣ ክቡር ብላታ ተክለ ወልደሐዋሪያትን ጨምሮ፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በወራሪ ኀይል ምክንያት አይሰደዱም በሚል ሐሳቡን አጥብቀው ተቃውመው እንደነበር ታሪክ ይናገራል፡፡
ንጉሱ በአውሮፓ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ሲመክሩ እና ለሀገራቸው ፍትሕ እንዲሰጥ ሲከራከሩ ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ደግሞ ለሀገራቸው ሰንደቅ ይዋደቁ ነበር፡፡
በመጨረሻም ጣሊያን የጀግኖቹን ትግል እና ቆራጥነት መቋቋም ሲያቅተው ኢትዮጵያን ለቆ ለመውጣት ተገደደ፡፡ ይህኔ ታዲያ ኢትዮጵያውያን ንጉሣቸውን ይቀበሉ ዘንድ ተዘጋጁ፡፡ ንጉሡም ለሀገራቸው ሲሠሩ የቆዩት የዲፕሎማሲ ሥራ ፍሬ በማፍራቱ እና ሀገራቸው ነጻ በመውጣቷ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡
ኢትዮጵያውያን አርበኞች ንጉሣቸውን የሚወዷትን ስንደቅ ይዘው ኦሜድላ በተባለው የኢትዮጵያ መሬት ላይ ጠበቋቸው፡፡ ንጉሡም ሲደርሱ ሰንደቁን ይሰቅሉ ዘንድ ቀረበላቸው፡፡ ንጉሡም የሚወዷትን የሀገራቸውን ሰንደቅ ከጀግኖቹ አርበኞች እጅ ተቀብለው በክብር ከፍ አደረጉ። ይህም የኾነው በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ባለውለታ ፕሬዚዳንት!
ጥር 12 ቀን 1953 ዓ.ም በዚህ ሳምንት የኢትዮጵያ ባለውለታ ጆን ፊዝጄራልድ ኬኔዲ (ጆን ኤፍ ኬኔዲ) 35ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኾነው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።
ይህ ሰው በኢትዮጵያ ብዙ የሚታወሱባቸው ነገሮች አሏቸው። ከእነዚህም መካከል የአዲስ አበባው ኬነዲ ቤተ መጽሐፍ የሚጠቀስ ሲኾን ፕሬዚዳንቱ እንዳስገነቡት የሚነገረው ይህ ቤተ መጽሐፍ ሁሌም የሚታወሱበት ነው፡፡
ኬኔዲ በሥልጣን በቆዩበት አጭር ጊዜ ውስጥ ቁጥራቸው ከ20 በላይ ነፃ የአፍሪካ ሀገር መሪዎችን ወይም አምባሳደሮቻቸውን በኋይት ሐውስ ተቀብለው አነጋግረዋል።
ፕሬዚዳንት ከመኾናቸው ከአንድ ዓመት በፊት 17 የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ገዥዎቻቸው ነፃነታቸውን አግኝተዋል።
ይህን ተከትሎም ዓለም እየተለወጠ መኾኑን የተገነዘቡት ኬኔዲ አዲስ ግንኙነት መመስረት እንደሚያስፈልግ በመገንዘብ ከአፍሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከፍ አድርገው እንደነበርም ነው የሚነገረው። ግንኙነቱ የተመሠረተውም አዲሶቹን የአፍሪካ ሀገራት በመደገፍ ነበር።
ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንደነበር እና በመጡበት ወቅትም በቤተ መንግሥት ውስጥ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎላቸው እንደነበርም ታሪካቸው ያትታል፡፡
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
