ከ24 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

53

እንጅባራ: ጥር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረስብ አሥተዳደር በተያዘው በጀት ዓመት ከ70 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ባለፉት 6 ወራት 24 ሺህ133 የሚኾኑ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ይህም በዓመቱ ከተያዘው ዕቅድ አንፃር 34 ነጥብ 1 በመቶ ነው።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና በሌሎችም ጉዳዮች በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት የተሠሩ ሥራዎችን ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በእንጅባራ ከተማ ገምግሟል። የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ ታፈረ ከበደ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

የተፈጠረው የሥራ ዕድል ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ካለው ሰፊ ፀጋ አንፃር በቂ አለመኾኑን ያነሱት መምሪያ ኀላፊው በቀሪ ወራት ሁሉንም ፀጋዎች አሟጦ በመጠቀም ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራም ገልጸዋል። ለሥራ ዕድል ለተፈጠረላቸው ወጣቶች የመሥሪያ እና የመሸጫ ቦታ እንዲሁም ከ 7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር እንደተመቻቸላቸውም አንስተዋል።

ለወጣቶች ለሥራ ማስጀመሪያ የሚሰጡ አጫጭር እና መደበኛ የክህሎት ሥልጠናዎች የወጣቶችን ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እንዲኾኑ በትኩረት እየተሠራ ነውም ነው ያሉት። የመድረኩ ተሳታፊዎችም አካባቢያቸው ባለው ፀጋ ልክ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሊባኖስ እና በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 359 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
Next articleየሰባር ጊዮርጊሥ ክብረ በዓል በባሕር ዳር በድምቀት ተጀምሯል።