የስንዴ ምርታማነት በምግብ ራስን ከመቻልም በላይ ነው።

32

ባሕር ዳር: ጥር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራትን ኢኮኖሚ በጽኑ መሠረት ላይ ለመመስረት እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል የስንዴ ምርት፡፡ ሀገራት ስንዴን ማምረት የሉዓላዊነት ማረጋገጫ አድርገው ሠርተዋል፡፡ በሠሩትም ሥራ ውጤት ማምጣት የቻሉ ሀገራት በርካታ ናቸው፡፡

በተለይም ቻይና፣ ሕንድ፣ ሩስያ እና አሜሪካ በየደረጃቸው ስንዴን በማምረት እና ለኢንደስትሪው በመመገብ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ሀገራት አሁን ላይ በገነቡት ኢኮኖሚ ኀያል ሁነው ዓለምን ለመዘወር እና እርስ በእርሳቸው ለመፎካከር በቅተዋል፡፡ የስንዴ ልማታቸው አድጎ ለታዳጊ ሀገራት በሚያቀርቡት የስንዴ ምርት የሀገራትን የውስጥ ጉዳይ ሳይቀር ለመዘወር እንዲዳዳቸው አድርጓቸዋል፡፡

እነዚህ ሀገራት ይህን የሚሠሩት እና በስንዴ ልማት የተሻለ ነገር መፍጠር የቻሉት እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ሀገራት በመሬት፣ በውኃ እና በሰው ኃይል የተሻለ ኾነው ሳይኾን ያላቸውን ግብዓት በሚገባ በመጠቀማቸው እና ዘመናዊ ቴክኖሎጅዎችን ጥቅም ላይ በማዋላቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አነሳሽነት የስንዴ ልማት በሀገሪቱ እንዲተገበር ተደርጓል፡፡

በወቅቱ በመንግሥት በኩል ትኩረት ቢሠጠውም በአርሶ አደሩ በኩል አዲስ ሀሳብ በመኾኑ እና ከነበረው አሠራር የተለየ በመኾኑ ተቀብለው የተገበሩት ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጅ የተዘራው ስንዴ ያስገኘውን ውጤት ተክትሎም አምራቹ አርሶ አደር አሁን ላይ ስንዴን ለመዝራት እና ከሚገኘው ገቢ ተጠቃሚ ለመኾን ያለው ተነሳሽነት ከፍ እያለ መጥቷል ይላል የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ፡፡

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ ውኃ አጠቃቀም ባለሙያ ንጋቴ ዓለማየሁ እንዳሉን እንደ ሀገር ስንዴን ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ድረስ ተደራሽ ለማድረግ እና የኢኮኖሚ አቅምን ለመገንባት ታሳቢ ተደርጎ እንደ የተለየ ዕቅድ ወጥቶ ከሦስት ዓመት በፊት ተግባራዊ ሲደረግ መቆቱን ነግረውናል፡፡

ስንዴን አምርቶ ወደ ውጭ በመላክ ሀገርን ከሌሎች ሀገራት ተርታ የማሰለፍ ሥራ አተገባር ላይ የኅብረተሰቡ አቀባበል እየጨመረ መምጣቱን ነው የነገሩን፡፡ እንደ ሀገር የተያዘውን የስንዴ ልማት ሥራ አማራ ክልልም ለመተግበር ሲንቀሳቀስ ቆይቷል የሚሉት ባለሙያው በውጤትም የተሻለ ነገር እየተገኘ ስለመኾኑ ነው ያብራሩት፡፡

አማራ ክልል በዚህ ዓመት 254 ሺህ 500 ሄክታር መሬትን በስንዴ ለመሸፈን ሲሠራ ስለመቆየቱ ነው የተናገሩት፡፡ ባለሙያው አሁን ላይ ክልሉ 237 ሺህ 387 ሄክታር መሬትን በመለየት ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 220ሺህ 883 ሄክታር መሬት ማረስ መቻሉን ነው ያብራሩት፡፡

191 ሺህ 384 ሄክታር መሬት አሁን ላይ በስንዴ ዘር ተሸፍኗልም ብለዋል፡፡ በሥራው ላይም 263 ሺህ 376 ኩንታል ስንዴ ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል ነው ያሉት፡፡ 8 ሚሊዮን 535 ሺህ 800 ኩንታል ለማግኘት እየተሠራ እንደኾነ የሚናገሩት ባለሙያው ይህም ውጤታማ እንዲኾን 305 ሺህ 773 ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እንደዋለም አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ ሥራ ላይ 541 ሺህ 681 አርሶ አደሮች ተሳታፊ ስለመኾናቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዘጋቢ: ምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleረቂቅ አዋጁ የመሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀምን በማዘመን ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።
Next article” 38ኛው አፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባኤን በላቀ ደረጃ ለማስተናገድ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ” አምባሳደር ብርቱካን አያኖ