“የማይሠራ ጉልበት፣ የማይለማ መሬት አይኖርም!”

31

ደባርቅ: ጥር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “የማይሠራ ጉልበት፣ የማይለማ መሬት አይኖርም!” በሚል መሪ መልዕክት ዞናዊ የተፈጥሮ ሃብትና ተፋሰስ ልማት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በሰሜን ጎንደር ዞን በየዳ ወረዳ ተካሂዷል። የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው አዳነ በዘንድሮው ዓመት የተፈጥሮ ሃብት እና ተፋሰስ ልማት መርሐ ግብር ከ18 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለማልማት መታቀዱን ገልጸዋል።

ከ300 በላይ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች እንደሚሠሩም ተናግረዋል። የተፈጥሮ ሃብትና ተፋሰስ ልማት ሥራው በሰባት ወረዳዎች እና አንድ ከተማ አሥተዳደር መጀመሩን አሳውቀዋል። በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሰሜን ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ደማሙ ሀብቴ የመሬት መራቆትን በዘላቂነት ለመከላከል እና የአርሶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻል የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

የበየዳ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሸጋው ብርሃኑ ወረዳው በተፈጥሮ ሃብት እና ተፋሰስ ልማት ጥሩ አፈፃፀም ማስመዝገቡን አስታውሰዋል። የወረዳው ነዋሪዎችም ላደረጉት ጉልህ አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ስለተፈጥሮ ሀብት ልማት እና እንክብካቤ ግንዛቤያቸው እያደገ መምጣቱን የአካባቢው አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ደብሬ ድሉ የተባሉ የበየዳ ወረዳ ዋቲ ቀበሌ ነዋሪ ከዚህ በፊት የተሠሩ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎችን ውጤታማነት በመመልከት በእኔነት ስሜት እየሠሩ እንደኾነ ገልጸዋል። ሌላው የቀበሌው ነዋሪ ቄስ ልጃለም በሪሁን የተሠሩ የተፈጥሮ ሀብትና ተፋሰስ ልማት ሥራዎችን በእርሻ ወቅት ከንክኪ በፀዳ መልኩ እየጠበቅን አዳዲስ የተፋሰስ ሥራዎችን እየሠራን ነው ብለዋል።

በዞኑ የተፈጥሮ ሀብትና ተፋሰስ ልማት መርሐ ግብር ከ170 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍል ይሳተፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ መምሪያው ገልጿል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበማዕድን ዘርፍ ከ19 ሺህ በላይ የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል።
Next articleጤናማ የሕይዎት ዘይቤን በመከተል እና መደበኛ የጤና ክትትል በማድረግ የጀርባ ሕመምን መከላከል ይገባል፡፡