
ደሴ: ጥር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ በምሥራቅ አማራ ለሚገኙት የማዕድን ሀብት ልማት መምሪያ፣ ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች በኮምቦልቻ ከተማ ሥልጠና እየሰጠ ነው። የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ታምራት ደምሴ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት “የማዕድን ሀብት ለኢንዱስትሪ፣ ለግብርና፤ ለመሠረተ ልማት መስፋፋት፤ የዉጭ ምንዛሬ ለማሳደግ፤ የዉጭ ምርትን በሀገር ዉስጥ በመተካት ለድህነት ቅነሳ እና ለሥራ ዕድል ፈጠራ አጋዥ መኾኑን ተናግረዋል።
በኮምቦልቻ ከተማ እየተሰጠ ያለው ሥልጠና ዘርፉን በእዉቀት መምራት የሚያስችል ቴክኒካል እዉቀት እና ክህሎትን ለማሳደግ፣ የአስተሳሰብ እና የአመለካከት እንድነት ለመፍጠር፣ አዲስ ወደ ዞን እና ወረዳ የሚወርዱ ተግባራትን የጋራ ለማድረግ እና በማዕድን ዘርፉ አዲስ ንቅናቄ ለመፍጠር ያለመ ሥልጠና ነው ብለዋል::
የደቡብ ወሎ ዞን ማዕድን ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ አሕመድ አበባው እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ማዕድን ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ሲራጅ ጀማል የማዕድን ዘርፍ ለኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰው በየአካባቢያቸው በርካቶች የሥራ እድል ተጠቃሚ እየኾኑ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አበባ ጌታሁን በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ 8 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ካፒታል ላላቸው 262 የማዕድን አልሚዎች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ በግማሽ ዓመቱ 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ላስመዘገቡ 104 አልሚዎች ፈቃድ ተሰጥቷል ብለዋል።
በዘርፉ ባለፉት ወራት ከ19 ሺ በላይ ለሚኾኑ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ እድል ተፈጥሯል ያሉት ወይዘሮ አበባ እሴት የተጨመረበት ኦፓል ወደ ውጪ በመላክ ከ882 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ተገኝተዋል ነው ያሉት። በኮምቦልቻ ከተማ እየተሰጠ ያለው ሥልጠና የባለሙያዎችን የክህሎት ክፍተት የሚሞላ እና ስለክልሉ የማዕድን አቅም ግንዛቤ የፈጠረ እንደኾነም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ከድር አሊ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
