
ደሴ: ጥር 16/2017 ዓ.ም( አሚኮ) የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ከክልሉ ምክር ቤት ጋር በመተባበር በገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በደሴ ከተማ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው። በምክክር መድረኩ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የገጠር መሬት አሥተዳደር አዋጅ ቁ/252 ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ነው ውይይቱ የሚካሄደው።
ረቂቅ አዋጁ የገጠር መሬትን ስለማግኘት፤ የገጠር መሬት ይዞታና አይነቶች፤ባለይዞታዎች በመሬታቸው የሚኖራቸው መብቶች፤ የገጠር መሬትን ስለመለካት፤ ስለመመዝገብ እና የምስክር ወረቀት ስለመስጠት ያካትታል። የወል መሬቶች እና አጠቃቀማቸው፤በገጠር መሬቶች ላይ ስለሚነሱ ክርክሮች፣ መፍትሔዎቹ፤ የገጠር መሬቶች ምዝገባ ፣ ቅየሳ እና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ ረቂቅ መኾኑም ተመላክቷል።
አዋጁ ሲጸድቅ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የገጠር መሬት እና በከተማ ከዚህ በፊት የነበሩ የሥራ ማነቆዎችን የሚፈታ እንደኾነ ተነስቷል። ረቂቅ አዋጁ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ሀገሪቱ ከደረሰችበት ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ጋር ለማዋሃድ አስፈላጊ ነው ተብሏል። የገጠር መሬት ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በአግባቡ ለማደራጀትም ሚናው ጉልህ እንደኾነ ተገልጿል።
የሀገሪቱን ስነ ምህዳር ያገናዘበ ዘላቂ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ለማውጣት እና ለማደራጀት፣ ሃብቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊ ነው ተብሏል። የመሬት አሥተዳደር ሥርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት ወሳኝ ሚና እንዳላቸውም ተገልጿል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች አዋጁ በተለይ በክልሉ በመሬት ዙሪያ የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች የሚፈታ መኾኑን ተናግረዋል። በአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አበራሽ ታደሰ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር አካል ጉዳተኞችን፣ ሕጻናት እና ሴቶችን በተለየ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ መኾኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሰይፉ ሰይድ በገጠርም ኾነ በከተማ ያለ የመሬት ሃብትን በአግባቡ እና በሕግ መምራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። አካታች የኾኑ ሕጎችን በማውጣት እና ለተፈጻሚነታቸው መትጋት ላይ የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ መኾኑንም ገልጸዋል። በምክክር መድረኩ የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሕግ ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ: ደምስ አረጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
