“የጸጥታ ኀይሉ በጽኑ መሠረት ላይ የቆመ የሕዝባችን ባለአደራ ነው” አቶ ደሳለኝ ጣሰው

36

ባሕር ዳር: ጥር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ባለፋት 6 ወራት ያከናወናቸውን የሕግ ማስከበር ሥራዎች በባሕር ዳር ከተማ እየገመገመ ነው። በግምገማው ላይ በየደረጃው ያሉ የክልሉ ሁሉም የጸጥታ ተቋማት መሪዎች እና የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በግምገማው የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አሥተባባሪ እና የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው ባለፉት 6 ወራት የተከናወኑ ዋና ዋና የሕግ ማስከበር ሥራዎችን አብራርተዋል። ያለፉት ስድስት ወራት የሕዝብን ሰላም ለማረጋገጥ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት። በዚህም በየጊዜው በሚፈጠር የጸጥታ መደፍረስ ሲቸገር የነበረው ሕዝባችን እፎይታን አግኝቷል ብለዋል።

አሁን ላይ የተገኘው ሰላም እንዲሁ የመጣ ሳይኾን ለሕዝብ እና ለሀገር በቆሙ ሁሉም የጸጥታ ተቋማት የቅንጅት ሥራ እና የሕይዎት መስዕዋትነት መኾኑን አንስተዋል። ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የክልሉን መንግሥት፣ ሕዝብ እና ሀገርን ምስቅልቅል ውስጥ ለማስገባት ያለመ ነበር ብለዋል። ይህንን እኩይ ድርጊት በመመከት ሕዝብ ሰላም ይኾን፣ ልማትም ይቀጥል ዘንድ የጸጥታ መዋቅሩ እስከመስዕዋትነት በሚዘልቅ ጽናት እና ርብርብ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን ጠቁመዋል።

ለሕዝብ እና ለሀገር ሲሉ ሰላምን ለማስፈን፣ በላብ ብቻ ሳይኾን በደም ጭምር ዋጋ የከፈሉ የክልል እና የፌዴራል የጸጥታ አባላት ምሥጋና ይገባቸዋል ብለዋል። ጥቅም ያላባዘነው፣ ፖለቲካ የማይነዳው፣ ይልቁንም ለሕዝብ ጥቅም ለአንድነት የቆመ፣ ጽንፈኝነትን የተጠየፈ እና በእሳት ተፈትኖ ያለፈ የጸጥታ ተቋም እና አባላት ገንብተናል ነው ያሉት። ይህ ኀይል በሁኔታዎች ያልተሸበረ፣ በጽኑ መሠረት ላይ የቆመ የሕዝባችን ባለአደራ ነው ሲሉም ተናግረዋል። በሕዝባችን ላይ የተጋረጠውን ዘርፈ ብዙ ፈተና ከፊት እየቀደመ ለሕዝብ እፎይታ የሰጠ ቁርጠኛ የሕዝብ ልጅ ነውም ብለዋል።

“የትላንትናው ፈተና ዛሬ በምናየው ብርሃን የሚረሳ መኾን የለበትም” ያሉት አቶ ደሳለኝ ሕዝባችን ከተጋረጠበት ፈተና እንዲሻገር፣ ቆሞ የቆየውን የኢኮኖሚ፣ የመሠረተ ልማት፣ የቱሪዝም እና የንግድ እንቅስቃሴ መልሶ እንዲያንሰራራ ለማድረግም ተጨማሪ የቤት ሥራዎች እንደሚቀሩም አመላክተዋል።

ከራስ በላይ ለሕዝብ ብሎ ዋጋ መክፈል የታሪክ ባላደራነት ነው ያሉት ኀላፊው የጸጥታ ኀይሉ ይህንን የሕዝብ አደራ ሲወጣ ቆይቷል፤ ለወደፊትም በጽናት ለመወጣት ዝግጁ ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾን የትውልድ ክፍተት የሚፈጥር ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢቲ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካን መርቀው ሥራ አስጀመሩ።