
አዲስ አበባ: ጥር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2017 የትምህርት ዘመን የስድስት ወር ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው። በዚሁ ግምገማ ላይ መነሻ ያቀረቡት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና ትምህርት ቢሮ ኀላፊ እና ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በዚህ ዓመት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ 7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ አቅዶ 40 በመቶ ብቻ መመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።
ይህ ማለት 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ያልተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር እንዳለ ያሳያል ነው ያሉት። ከዚህ ውስጥ 400ሺህ ያክል ከተመዘገቡ በኋላ ወደ ትምህርት ገበታ እንዳልገቡ አብራርተዋል። በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ደግሞ 136 ሺህ ተማሪዎች ትምህርት ቤት የፈረሰባቸው በመኾኑ የትምህርት ቤት አልሄዱም ነው ያሉት።
ባለፈው ዓመት 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ዕቅድ ቢዬዝም በዓመቱ ውስጥ ማስተማር የተቻለው 58 በመቶ የሚኾነውን ብቻ ስለመኾኑም አብራርተዋል። አትራፊው ማነው ብሎ መጠየቅ ይገባል ያሉት ቢሮ ኀላፊዋ ተስፋ አንቆርጥም ለቀጣይም ለመመዝገብ አንጥራለን ነው ያሉት።
አሁን ላይ አንዳይማሩ በመደረጋቸው ከቴክኖሎጅ እና ከዓለም እንዳይገናኙ እየተደረገ ነው ሲሉ ነው ያለውን ችግር ያስገነዘቡት። ዛሬ ካላስተማርን ሀገር ገንቢ ትውልድ፤ ቤት ገንቢ ኢንጂነር፤ ፖለቲከኛ እና ሥራ ፈጣሪ አዕምሮዎች ያሳጣናል ብለዋል። የትውልድ ክፍተት እየተፈጠረ ነው ሲሉም ተናግረዋል። የትውልድ ክፍተት ደግሞ በተውሶ የማይሞላ ከባድ ውድቀት የሚያመጣ የነገን ጉዞ የሚያደበዝዝ ሲሉ ነው የችግሩን ስፋት ያብራሩት።
ትምህርት ባለመኖሩ ተማሪዎች ለስደት፣ ለያለዕድሜ ጋብቻ፣ ለጾታዊ ጥቃት እና ለተስፋ መቁረጥ እንዲጋለጡ ኾነዋል ነው ያሉት። እንደ ዶክተር ሙሉነሽ ማብራሪያ ይህንን ተረድቶ መላው የትምህርት ማኅበረሰብ እና መሪዎች ከሕዝቡ ጋር በመኾን ሊያወግዙ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በቢሮው የዕቅድ ዝግጅት እና ፕሮጀክት ክትትል ዳይሬክተር ዘመነ አበጀ አንዳሉት 97 የቅደመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 3ሺህ 182 የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 97 የሁለተኛ እና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች በጠቅላላ 3ሺህ 337 ትምህርት ቤቶች ለትምህርት በራቸውን አልከፈቱም።
ይህ ደግሞ ያልተመዘገቡ 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ተመዝግበው ወደ ትምህርት ቤቶቻቸው ያልመጡ 400 ሺህ በላይ ተማሪዎች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ 106 በሀገርነት ከተመዘገቡ ሀገራት የሕዝብ ቁጥር የሚበልጥ እንደኾነም ነው ያብራሩት። ይህ ደግሞ የአማራ ክልልን ብቻ ሳይኾን ኢትዮጵያን አንደሀገር ከባድ ችግር የሚከት በመኾኑ ሁሉም ሊያሳስበው ይገባል ብለዋል።
በክልሉ በሰሜኑ ጦርነት ከወደሙ ከ4ሺህ 200 በላይ ትምሀርት ቤቶች 10 በመቶ ብቻ ምላሽ ያገኙ ሲኾን በአሁኑ በክልሉ ውስጥ ባለው ጦርነት ደግሞ በከፊል እና በሙሉ 2 ሺህ ትምህርት ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።
በክልሉ አስከአሁን 46 ትምህርት ቤቶች እና 243 የመማሪያ ክፍሎች ሙሉ በሙሉ የዳስ ሲኾኑ 13 በመቶ ብቻ ደረጃቸውን የጠበቁ መኾናቸውን የቢሮው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
