በየዓመቱ ከአራት ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ተገንብቷል።

22

ባሕር ዳር: ጥር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጉባኤ በኋላ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና ክህሎት ልማት ዘርፍ በተሠሩ ሥራዎች እና ውጤቶች ዙሪያ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም እያደገ የመጣውን የሥራ ዕድል ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የ10 ዓመት ዕቅድ ተነድፎ ሥራ ላይ መዋሉን አስታውሰዋል። በዚህም በየዓመቱ 2 ሚሊዮን የሥራ ዕድል በመፍጠር በዕቅዱ መጨረሻ 20 ሚሊዮን ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ መያዙን አንስተዋል።

ነገር ግን አዳዲስ እሳቤዎች ገቢራዊ በመደረጋቸው ከዕቅዱ በላይ በመፈጸም በየዓመቱ በአማካይ ከ4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል እየተፈጠረ መኾኑን አንስተዋል። ለውጡን ተከትሎ ተግባራዊ የተደረጉ አዳዲስ ዕሳቤዎችን መሠረት በማድረግ ዕቅዱ ላይ ክለሳ መደረጉን ጠቁመው ይህም በሀገር ደረጃ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅምን ማሳደጉን ተናግረዋል።

የክህሎት እና ፈጠራ መር ኢኮኖሚ ለመገንባት አዳዲስ አሠራሮች መዘርጋታቸውን ገልጸው ይህም በመስኩ ስኬታማ ሥራዎችን ለማከናወን ማስቻሉንም አስረድተዋል። እንደ ሚኒስትር ሙፈሪሃት ገለጻ የሥራ ዕድል ፈጠራ አቅምን ውጤታማ ለማድረግ ተግባራዊ በተደረጉ የብልጽግና እሳቤዎች በየዓመቱ ከአራት ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን ዜጎች የውጭ ሀገር ኩባንያዎችን ሥራ መሥራት የሚችሉበት ዕድል መመቻቸቱን የገለጹት ሚኒስትሯ በአጭር ጊዜ ከ80 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል መፈጠሩን አመልክተዋል። የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪትን ውጤታማ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የታገዘ ተግባር እየተከናወነ መኾኑንም አብራርተዋል።

በውጭ ሀገራት ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች ተገቢውን ክህሎት እንዲጨብጡ እና በሥነ ልቦና ተዘጋጅተው እንዲሄዱ እየተደረገ ነው ብለዋል። ከለውጡ በኋላ በተዘረጋው የድጋፍ እና ክትትል አሠራር ወደ ውጭ ለሥራ የሚሰማራው ዜጋ ቁጥር እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል። የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማትን የማጠናከር እና የቅበላ አቅማቸውን የማሳደግ ሥራ መሠራቱንም አስረድተዋል።

በዚህም ተቋማቱ በአጫጭር እና መደበኛ የሥልጠና መስኮች 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን በየዓመቱ ተቀብለው የማሠልጠን አቅም መፍጠራቸውንም አብራርተዋል። እንደ ኢዜአ ዘገባ በየአካባቢው ያሉ ጸጋዎችን ማየት እና መጠቀም እንዲሁም ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር ላይ ትኩረት ያደረገው የለውጥ እሳቤ ለተገኙ ስኬቶች መሠረት መጣሉንም አመልክተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መሬት የመልካም አሥተዳደር ችግር ምንጭ እንዳይኾን በሕግ እና ሥርዓት ማሥተዳደር ይገባል” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)
Next articleየተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾን የትውልድ ክፍተት የሚፈጥር ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)