
ባሕር ዳር: ጥር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ከክልሉ ምክር ቤት ጋር በመተባበር በገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
በውይይት መድረኩ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ጨምሮ የምክር ቤት አባላት እና የቢሮ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በቴክኖሎጂ የታገዘ የመሬት አሥተዳደር ሥርዓትን መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል። ያደጉት ሀገራት የገቢ ምንጫቸው መሬት መኾኑን ያነሱት ኀላፊው መሬትን በአግባቡ ማሥተዳደር ተገቢ ነው ብለዋል።
መሬት የመልካም አሥተዳደር ምንጭ እንዳይኾንም በሕግ እና ሥርዓት ማሥተዳደር አስፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል። የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ ቢሮው የአርሶ አደሮችን የይዞታ መብት የማረጋገጥ ሥራ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ማንኛውም አርሶ አደር የገጠር መሬቱን ለግብርና ተግባር የማዋል፣ ለቤተሰብ አባል የማውረስ፣ በጉልበቱ ወይም በገንዘቡ አልምቶ ንብረት ማፍራት የይዞታ መብት እንዳለውም ገልጸዋል። ከባለሀብት ጋር በጋራ መሬቱን ማልማትም ይችላል ነው ያሉት።
ረቂቅ አዋጁ ከዚህ በፊት ይሰራባቸው የነበሩ ሕጎች አሁን ወቅቱን የዋጁ እንዲኾኑ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
